የግድቡ ግንባታ የተለያዩ ጫና እና መሰናክሎች ቢገጥሙትም በስኬት አሁን ላለበት ደረጃ በቅቷል- ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ - ኢዜአ አማርኛ
የግድቡ ግንባታ የተለያዩ ጫና እና መሰናክሎች ቢገጥሙትም በስኬት አሁን ላለበት ደረጃ በቅቷል- ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ
ነሐሴ 05 ቀን 2014(ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ የተለያዩ ጫና እና መሰናክሎች ቢገጥሙትም በስኬት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረሱን የግድቡ ግንባታ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመሩን አብስረዋል።
በመርሐግብሩ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዚህ ወቅት መልእክት ያስተላለፉት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፤ በግድቡ በ2014 ዓ.ም ለማከናወን ከተያዙ አብይ እቅዶች መካከል በሁለት ተርባይንና ጄነሬተሮች ኃይል የማመንጨት ሥራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የግድቡ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ እቅዱን ማሳካት መቻሉን በተግባር ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
ከለውጡ በኋላ በፕሮጀክቱ ላይ የማስተካከያ እርምጃዎች ተደርገው ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
የግድቡ ግንባታ አሁን ላይ የሲቪል ግንባታ ሥራው 95 በመቶ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ተከላ ሥራ 61 በመቶ እንዲሁም የውሃ ማስተላለፊያ የብረታ ብረት ሥራም 73 በመቶ ደርሷል ብለዋል።
በዚህም የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በአጠቃላይ ወደ 83 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱን ነው የተናገሩት።
በቀጣይ ሁለት ዓመታት ግድቡን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ የታለመለትን ኃይል እንዲያመነጭ ለማድረግ ፕሮጀክቱ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ከውስጥም ከውጭም ፈተና የበዛባት መሆኑንና የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትንም ለማሰናከል ብዙ ጥረት መደረጉን አስታውሰዋል።
የፕሮጀክቱን ግንባታ ለማደናቀፍ ብዙ ጥረት ቢደረግም በሕዝቡና መንግሥት ብርቱ ትብብር የግድቡ ግንባታ ሳይደናቀፍ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረስ መቻሉን ነው የተናገሩት።