የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት አሁን የደረሰበት ስኬት የኢትዮጵያን ብልጽግና ማንም ማስቆም እንደማይችል ማሳያ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት አሁን የደረሰበት ስኬት የኢትዮጵያን ብልጽግና ማንም ማስቆም እንደማይችል ማሳያ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
ነሐሴ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት አሁን የደረሰበት ስኬት የኢትዮጵያን ብልጽግና ማንም ማስቆም እንደማይችል ማሳያ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባ በመገኘት የግድቡ ሁለተኛ ተርባይን ሃይል ማመንጨት መጀመሩን ባበሰሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልእክት በዚህ ታሪክ ውስጥ ማለፍ ዕድል ብቻ ሳይሆን ድልም ስለመሆኑ ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያዊያን ባለእድልም፤ ባለድልም ሆነናል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዚህ ዕድልም ድልም ተቋዳሽ በመሆናችን ትልቅ ደስታ ይሰማናል ብለዋል።
ከአባይ ለመጠቀም ቀደምት አባቶቻችን ብዙ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቆይቶ አሁን ላይ ለዚህ ድል በቅተናል ነው ያሉት።
በመሆኑም "አባቶቻችን ብዙ የለፉበትንና በሃሳብ ደረጃ ያለውን እኛ ወደ ተግባር ቀይረንዋል፤ በዚህም አይቻልም የተባለውን ተችሎ አይተንዋል'' ብለዋል።
ይህ እውን እንዲሆን ኢትዮጵያውን ገንዘባቸውን ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸውን ጭምር መክፈላቸውን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ለላቀ ድል መነሳሳት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጸናችና የበለጸገች አገር ለማቆየት መትጋት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የታችኛው ተፋስስ አገራትም ቢሆኑ ኢትዮጵያ የሃይል ፍላጎቷን ከማሟላት ባለፈ የተለየ ዓላማ እንደሌላት ሊረዱ ይገባል ብለዋል።
ለዚህም የእስካሁኑ የግንባታ ሒደት ማረጋገጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ ያለውን ሁኔታ በንግግር ለመፍታት እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያውን ለዚህ ውጤት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ለተገኘው ስኬትም እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤