ቀጥታ፡

የአባቶችን ህልም እና ፍላጎት እውን በማድረግ ሀገርን በፀና መሰረት ላይ ማቆም የዚህ ትውልድ ሃላፊነት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

ነሐሴ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአባቶችን ህልም እና ፍላጎት እውን በማድረግ ሀገርን በፀና መሰረት ላይ ማቆም የዚህ ትውልድ ሃላፊነት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የህዳሴ ግድብ 2ኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመር ማብሰሪያ ሥነ ስርአት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 2ኛ ተርባይን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት በይፋ መበሰርን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት የህዳሴ ግድብ እውን መሆን በርካታ ዋጋ ተከፍሎ ተረት የነበረው ግድብ ታሪክ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ትውልዱ አባቶች ያሰቡትን ህልም እና ፍላጎት እውን በማድረግ ሀገርን በፀና መሰረት ላይ የማቆም ሃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በታሪክ ውስጥ ማለፍ እና ታሪክ መስራት ይለያያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “በታሪክ ውስጥ ማለፍ እድል፤ ታሪክ መስራት ደግሞ ድል ነው” ብለዋል።

ቀደም ባሉ ግዚያት የቁጭት ዘፈኖችና ተረቶች ሲያስተናግድ የነበረው የህዳሴ ግድብ እውን ሆኖ ወደ ታሪክነት ተቀይሯል ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

በዛሬው እለት ስራ የሚጀምረው ዩኒት ዘጠኝ ሲሆን፥ 270 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ተጠቅሷል፡፡

ባለፈው የካቲት ወር ላይ 270 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ዩኒት10 ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዛሬውን ጨምሮ በአጠቃላይ 540 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም