የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ለተያዘው የስራ ዘመን ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አፀደቀ

99

ቦንጋ፣ ነሐሴ 04/2014 (ኢዜአ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ለተያዘው የስራ ዘመን ማስፈጸሚያ እንዲውል ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ አፀደቀ።

በቦንጋ ከተማ ቀጥሎ ባለው የምክር ቤቱ  መደበኛ ጉባኤ ላይ  የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ወሰነች ቶማስ እንዳስረዱት፤በጀቱ ከክልሉ መንግስት ከሚሰበሰበው የውስጥ ገቢ፣ ከፌደራል መንግስት ድጎማ እና ከሌሎች የገቢ ምንጮች የሚሸፈን ነው።

በጀቱ በክልሉ ለሚገኙ ዞኖችና የክልል ማዕከላት ከፋፍሎ  ለመመደብ  ቀመርና ሌሎች መመዘኛዎችን መሰረት በማድረግ መሠራቱንም ገልጸዋል ።

ይህንን መሰረት በማድረግ ለተያዘው የስራ ዘመን ማስፈጸሚያ እንዲውል የቀረበውን ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ረቂቅ የበጀት አዋጅ ላይ ምክር ቤቱ ከተወያየበት በኋላ  በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

በክልሉ የሚገኙ ዞኖች በጀቱን ለወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ፍትሀዊ በሆነ መልኩ የማከፋፈል ስራ እንደሚጠበቅባቸው ተመልክቷል።

በዚህም ያልተማከለውን የፋይናንስ አስተዳዳር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም