በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚስተዋሉ የወንጀል እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ሕዝቡ ከፖሊስ ጎን መሆን አለበት- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

50

ነሃሴ 04 ቀን 2014(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚስተዋሉና ትኩረት የሚሹ የወንጀል እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ሕዝቡ ከፖሊስ ጎን መሆን እንዳለበት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከተማ አስተዳደሩ በሶስት ክፍለ ከተሞች ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ዘመናዊ የፖሊስ መምሪያ ሕንፃዎችንና ሌሎች ፕሮጀክቶችን አስመርቋል።

ለምረቃ የበቁት የፖሊስ መምሪያ ህንፃዎች በአራዳ፣ ልደታና ኮልፌ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ሲሆን በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ደግሞ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ፣ የምገባ ማዕከላትና ሌሎች ፕሮጀክቶች ናቸው።

የመዲናዋ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ የከተማ አስተዳደሩ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በመፈፀም ለአገልግሎት ብቁ እያደረገ ነው ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም በመዲናዋ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከ100 በላይ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተመረቁ ፕሮጀክቶች የመዲናዋ ነዋሪዎች የረጅም ጊዜ ጥያቄዎች የነበሩ ሲሆን መንግስት በምርጫ ወቅት በገባው ቃል መሰረት ምላሽ እየሰጠባቸው መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

የተጠናቀቁ የፖሊስ ተቋማት ትርጉም ባለው መልኩ ዘመናዊና ውጤታማ የፖሊስ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዙም አንስተዋል።

በአንጻራዊነት የአዲስ አበባ ከተማ የተሻለ መሆኑን ጠቅሰው አሁንም ትኩረት የሚፈልጉ የወንጀል እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

እነዚህን የወንጀል እንቅስቃሴዎች ለመግታትና የመዲናዋን ሰላምና የነዋሪውን ደህንነት ለማረጋገጥ የፖሊስ ሰራዊቱ እያካሄደ የሚገኘውን ተግባር አድንቀው፤ ህብረተሰቡም በዘርፉ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፤ በበኩላቸው የፖሊስ ሰራዊቱ ከመዲናዋ ነዋሪዎች ጋር በመተባበር የፀረ ሰላም ሃይሎችን ሴራ እያከሸፈ መሆኑን ተናግረዋል።

May be an image of 1 person and text that says "AMN etv"

በዚሁ ተግባርም የከተማዋን ሰላም አስተማማኝ ማድረግ እንደተቻለ ጠቁመው፤ በዛሬው ዕለት የተመረቁት ህንፃዎችም ለሰራዊቱ ምቹ የስራ ቦታን በመፍጠር ውጤታማ ስራ ለማከናወን ይረዳሉ ብለዋል።

በቀጣይ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተመሳሳይ የፖሊስ ተቋማት እንደሚገነቡ የገለጹት ኮሚሽነሩ የከተማ አስተዳደሩም የፖሊስ ተቋሙን ለማጠናከር እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል ረዲ፤ ፕሮጀክቶቹ በስራ ዕድል ፈጠራ እና ሌሎች ዘርፎች ላይ አገልግሎት በመስጠት የዜጎችን ተጠቃሚነት ያሳድጋሉ ብለዋል።

May be an image of 2 people

በክፍለ ከተማውም ፖሊስ መምሪያ፣ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያን ጨምሮ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ከ160 በላይ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

በፕሮጀክቶቹ ምረቃ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ለዚሁ ስኬት አስተዋጽኦ የነበራቸው አካላትም እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም