ቀጥታ፡

በምርት ዘመኑ በገበያ ተኮር ኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ የተሰባሰቡ አርሶ አደሮችን ቁጥር ወደ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ለማሳደግ ታቅዷል

ነሃሴ 4/2014/ኢዜአ/ በ2014/2015 የምርት ዘመን ገበያ ተኮር ኩታ ገጠም አስተራርስ ዘዴ የተሰባሰቡ አርሶ አደሮችን ቁጥር ወደ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ለማሳደግ መታቀዱን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለፀ።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ይፍሩ ታፈሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ክላስተር ወይም የገበያ ተኮር ኩታ ገጠም እርሻ ለግብርናው ዘርፍ ሽግግር አይነተኛ መፍትሔ ነው።

ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ የብቅል ገብስና ሰሊጥ ከእህል ዘር፤ አቡካዶ፣ ማንጎ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና የሙዝ ሰብሎች ደግሞ ከአትክልትና ፍራፍሬ ዘር በክላስተር እርሻ እየተሰራባቸው ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአራት ክልሎች የሚገኙ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን አርሶ አደሮች በ300 ወረዳዎች በክላስተር አስተራረስ ዘዴ መታቀፋቸውን ገልፀው፤ አሁን ላይ ወደ ስድስት ክልሎች መስፋቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም በ2014 ዓ.ም ከትግራይ ክልል ውጭ ባሉና ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው ክልሎች የነበረው አፈጻጸም አበረታች እንደነበር ተናግረዋል።

በምርት ዘመኑም ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በክላስተር እርሻ ለመሸፈን ታቅዶ 90 በመቶውን ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በክላስተር የአስተራረስ ዘዴ ከታቀፉት ከ300 ወረዳዎች በተጨማሪ የአርሶ አደሮች ምርት 'ክላስተር' የሚሰኝ ፕሮጀክት ትግበራ ላይ ነው ብለዋል።

በዚህ ፕሮጀክትም ኩታ ገጠም ማሳ ያላቸው እስከ 50 የሚደርሱ አርሶ አደሮች በፈቃደኝነት ተሰባስበው በጋራ እንዲያዘምሩ ይደረጋል ነው ያሉት።

የእነዚሁ አርሶ አደሮች ስብስብ በአምስት ዓመታት ውስጥ አደረጃጀታቸውን ወደ ዘመናዊ የአርሶ አደሮች እርሻ ድርጅት የማሳደግ ዓላማ እንዳለም በመግለጽ።

አርሶ አደሮቹ ግብዓትና ስልጠና እየቀረበላችው የሚያስፈልግውን መስፈርትና ደረጃ ሲያሟሉ ወደ ኩባንያ እንዲያድጉም ይደረጋል ነው ያሉት።

በ2014 በጀት አመት ማጠናቀቂያ ድረስ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን በዚህ አሰራር ለማሰባሰብ መቻሉንም ተናግረዋል።

በቀጣዩ የ2015 በጀት ዓመት ደግሞ የእነዚህን አርሶ አደሮች ቁጥር ወደ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ለማሳደግ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹ ሰብላቸውን የሚያመርቱት በፈረቃ መሆኑን ገልጸው፤ ለዘይት ምርት ኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የቅባት እህሎችን በኩታ ገጠም እርሻ ማዝመር መጀመሩን ገልጸዋል።

በዚህም አማራ ክልል ብቻ በአኩሪ አተር ባለፈው አመት 89 ሺህ ሄክታር መሬት በገበሬዎች የምርት ክላስተር እንደተጀመረ አውስተዋል።

በዘንድሮው ምርት ዘመን ደግሞ 250 ሺህ ሄከታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እስከሁን ከ230 ሺህ ሄክታሩ በዘር ተሸፍኗል ነው ያሉት።

ይህ አይነቱ አሰራር በኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም