በክልሉ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ካምባኒዎች በማዕድን ዘርፍ ተሰማርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ካምባኒዎች በማዕድን ዘርፍ ተሰማርተዋል
ባህርዳር፤ ነሐሴ 4/2014 (ኢዜአ)፡ በአማራ ክልል ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ካምፓኒዎች በማዕድን ኢንቨስትመንት ዘርፍ የምርመራና ማምረት ስራ ፈቃድ ወስደው እየሰሩ መሆናቸውን የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ኃይሌ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ያለውን ዕምቅ የማዕድን ሀብት በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ቢሮው በትኩረት እየሰራ ነው።
ለዚህም ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ብቻ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 102 ካምፓኒዎች በማዕድን ዘርፍ የምርመራና ማምረት ስራ ፈቃድ ወስደው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የተለያዩ ፋብሪካዎች ለወለል ንጣፍ፣ ለደረጃና ሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ግራናይት፣ ማርብልና ጂብሰም እያመረቱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ካምፓኒዎቹ በዓመት እስከ 130 ሺህ ቶን ግራናይት ማርብልና ጅብሰም አምርተው ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን አመልክተው፤ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች የመተካት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የምርመራ ፈቃድ ከወሰዱ ሰባት የስሚንቶና 30 የድንጋይ ከሰል ካምፓኒዎች 3ቱ የምርመራ ስራቸውን ማጠናቀቃቸውን ገልጸው፤ የማምረት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን አመልክተዋል።
በማዕድን ዘርፍ የምርመራና የማምረት ፈቃድ የወሰዱት ካምፓኒዎች ከ23 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠራቸውንም አቶ ኃይሌ አስታውቀዋል።
ሀገሪቱ በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ወደ ከፍታ ከምትወጣባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ ማዕድን ነው'' ያሉት አቶ ኃይሌ፤ የክልሉ መንግስትም ለዘርፉ ዕድገት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የቤአይካ ጄኔራል ቢዝነስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ምስጋናው በበኩላቸው ኩባንያቸው 10 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ካፒታል በንግድ፣ ኢንዱስትሪ፣ እርሻና ኮንስትራክሽን ዘርፎች ተሰማርቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ በማዕድን ዘርፍ ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚውሉ ግራናይት፣ ማርብል፣ ታይልስና ካልሽየም በሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ መቶ በመቶ እያመረቱ መሆኑን አስረድተዋል።
አሁን ላይ ግራናይት 3 ሺህ 500 ካሬ፣ ማርብል 1 ሺህ ካሬ፣ ታየርስ 2 ሺህ 500 ካሬ፣ ቀለም 100 ሺህ ሊትር በቀን በማምረት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ምርቱን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በሀገር ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ከመጭው ጥቅምት ወር ጀምሮ የግራናይት ምርትን በ3 ዕጥፍ፣ የማርብል ምርትን ደግሞ በሁለት ዕጥፍ የሚያሳድጉ ተጨማሪ ፋብሪካዎችን ለመትከል የተገዙ ማሽነሪዎችን እያጓጓዙ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም ለኤክስፖርት ብቻ የሚሆን የግራናይት ምርት የሚያመርት ግዙፍ ፋብሪካ ጥሬ ዕቃው በሚገኝበት በምዕራብ ጎጃም ቡሬ አካባቢ ለመትከል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
''መንግስትም 24 ሰዓት ፋብሪካዎቻችን ስራቸውን ሳያቋርጡ እንዲያከናውኑ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማቅረብ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎች እያደረገልን ነው'' ብለዋል።
ኩባንያው በተሰማራባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለ7 ሺህ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ 40 በመቶው በማዕድን ዘርፍ የተፈጠረ ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል ለኢንዱስትሪ፣ ለኮንስትራክሽን፣ ለብረት፣ ለኃይል አቅርቦትና ለጌጣጌጥ የሚውሉ 35 አይነት ማዕድናት እንደሚገኙ በጥናት መረጋገጡን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።