ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ በሰላምና አብሮነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል

ሐረር፤ ነሐሴ 4/2014 (ኢዜአ)፡ የሐረሪ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በሰላምና አብሮነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታወቀ።

የሐረሪ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሐምሌ 30/2014 ዓ.ም ያካሄደውን መደበኛ ጉባኤ ተከትሎ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼክ አብዱሰላም ጂብሪል  በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት ምክር ቤቱ ባካሂደው መደበኛ ጉባኤ  ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ምክርቤቱን የሚመሩ 14 ከፍተኛ አመራሮች መመረጣቸውን አስታውቀዋል፡፡

''ምክር ቤቱ ያካሄደው ጉባኤ ሁሉን አቀፍ እና አሳታፊ ነበር'' ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤  አዲሱ የምክር ቤቱ አባላት ማህበረሰቡን በማስተባበር  ለሰላም አብሮነት ትኩረት  በመስጠት  ይሰራሉ ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ የክልሉን መጅሊስ አደረጃጀት ወደ ታች  በማውረድ የማህበረሰቡ እምነት ነክ ጥያቄ   በኡለማዎች እንዲፈቱ እንደሚሰራም ገልጸዋል ፡፡

 ''የለውጡ መንግስት  የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የተቋማቸው ባለቤት እንዲሆኑ አድርጓል'' ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው  መንግስት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በቅርቡ የፌዴራል መጅሊስ አባላትን በመጋበዝና የክልሉን ህዝብ በማስተባበር 10 ሺህ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን አመልክተው፤ በደም እጦት ህወታቸው የሚያልፍ  ወገኖች ህወትን ለመታደግ  ከ 3 ሺህ በላይ ሰዎችን  ያሳተፈ  የደም ልገሳ መርሐ ግብርም  ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡

የምክር ቤቱ አባላት ለማህበረሰቡ አንድነት እና ለሀገር ሰላም ትኩረት በመስጠት የወንድማማችነት መንፈስን በማጎልበት ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም