ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል በስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ጉዳት ያደረሱ የሙርሌ ታጣቂዎች ላይ ክትትል እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ነሐሴ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በዲማ ወረዳ የኡኩጉ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ጉዳት ያደረሱ የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ታጣቂዎች ላይ ክትትል እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰናይ አኩዎር ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ ታጣቂዎቹ ጉዳቱን ያደረሱት ነሐሴ 02 ቀን 2014 ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ወደ መጠለያ ጣቢያው ሰርገው በመግባት በሴቶችና ህፃናት ላይ በፈጸሙት ጥቃት ነው።

ታጣቂዎቹ በፈጸሙት ጥቃት የሁለት ሰዎች ህይወት እንዳለፈና አንድ ሰው ደግሞ በጽኑ መቁሰሉን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ሁለት ህፃናት በታጣቂዎቹ ታፍነው መወሰዳቸውን ጠቁመዋል።

የጸጥታ ኃይሎች በፍጥነት ደርሰው ጥቃቱን ባይከላከሉ ኖሮ የከፋ ጉዳት ሊደርስ ይችል እንደነበር ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም በቂ የጸጥታ ኃይል በአካባቢው በማሰማራት ለስደተኞች አስፈላጊው ጥበቃ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተው፤ ጉዳቱን ያደረሱ ታጣቂዎች ላይ አስፈላጊው ክትትል እየተደገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የሙርሌ ታጣቂዎች ከሁለት ሳምንት በፊት በዚሁ ወረዳ በሚሊሻ የጸጥታ አካላት ጥቃት ለማደረስ ሙከራ አድረገው እንደነበር አስታውሰዋል።

የክልሉ መንግስት የሙርሌ ታጣቂዎቹ በተደጋጋሚ እየሞከሩ ያለውን ህፃናትን አፍኖ የመውሰድና የቀንድ ከብት ዘረፋ ወንጀሎ ለመከላከል በመግቢያቸው አካባቢ የጸጥታ አካላትን የማጠናከር ስራ እያከናወነ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስታቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም