ክልሉ በ2014 የምርት ዘመን ከ64 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ አቅርቧል-ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

84

ነሐሴ 3 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በ2014 የምርት ዘመን ከ64 ሺህ ቶን በላይ የታጠበና ያልታጠበ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡ ተገለጸ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ይህን የገለጹት የክልሉ ምክር ቤት ቦንጋ ከተማ እያካሄደ ባለው 6ኛ ዙር 1ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የ2014 በጀት ዓመት የተግባር አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው።

ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እንዳሉት በ2014 የምርት ዘመን 221 ነጥብ 7 ሺህ ቶን አጠቃላይ የቡና ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ 239 ነጥብ 7 ሺህ ቶን የቡና ምርት መሰብሰብ ተችሏል።

ከዚህም ምርት ውስጥ 61 ሺህ 864 ቶን የቡና ምርት ለገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ከዕቅድ በላይ 64 ሺህ 470 ቶን ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።

ለማዕከላዊ ገበያ ከቀረበው የቡና ምርት ከ20 ሺህ ቶን በላይ ምርት የታጠበ መሆኑን አብራርተዋል።

ሕገ ወጥ የግብይት እንቅስቃሴን ለመከላከል በተደረገው ጥረት ከ170 ቶን በላይ ሕገ ወጥ ቡና በመያዝ ከ15 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

በክልሉ በ2013 ዓ/ም የነበረውን 541 ሺህ ሄክታር የቡና ማሳ ሽፋን ወደ 559 ሄክታር ማሳደግ መቻሉ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም