ኬንያውያን ፕሬዝዳንታቸውን እየመረጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኬንያውያን ፕሬዝዳንታቸውን እየመረጡ ነው

ነሐሴ 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኬንያውያን ለቀጣይ አምስት ዓመት የሚመራቸውን ፕሬዝዳንት በመምረጥ ላይ ናቸው።
የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ልዑክን በመምራት ምርጫውን በመታዘብ ላይ ናቸው።
ዛሬ እየተካሄደ ባለው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ድምጽ ለመስጠት መመዝገባቸውን የአገሪቷ ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።
ኬንያውያን ከማለዳ 12 ሰአት ጀምሮ ድምጻቸውን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ የኬንያው ዴይሊ ኔሽን ዘገባ ያመለክታል።
ለኑሮ ውድነትና ለሸቀጦች ዋጋ ንረት መፍትሄ፣ ሙስናን መዋጋት እንዲሁም ዜጎችን ከድህነት ማውጣት ሌሎች ተጓዳኝ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የመራጮች ዋንኛ ትኩረት መሆናቸው ተገልጿል።

የቀድሞ የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ፣ የወቅቱ የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ ዴቪድ ዋይሂጋ እና ጆርጅ ዋጃኮያህ በምርጫው ላይ የሚሳተፉ እጩዎች ናቸው።
የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አገሪቷ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን እ.አ.አ 1991 ካስተዋወቀች በኋላ ለአምስተኛ ጊዜ የሚከናወን ነው።
የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ልዑክ በመምራት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን እየታዘቡ ነው።
የኢጋድ የአጭር ጊዜ ታዛቢ ልዑክ ኬንያ ባቀረበችው ጥያቄ አማካኝነት የተቋቋመ ሲሆን ሰባት ቁልፍ የሚባሉ አባላት (ኮር ስታፍ) እና 24 የአጭር ጊዜ የምርጫ ታዛቢዎችን አካቷል።
የአፍሪካ ሕብረት እና የአውሮፓ ሕብረት ጨምሮ ሌሎች አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ምርጫውን በመታዘብ ላይ ይገኛሉ።
መራጮች እስከ ቀኑ 11 ሰአት ድረስ ድምጻቸውን መስጠት እንደሚችሉ ተገልጿል።
የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን በመጀመሪያ ዙር ለማሸነፍ አንድ እጩ ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ እና በአገሪቷ ከሚገኙ 47 ግዛቶች ውስጥ በ24ቱ በትንሹ 25 በመቶ ድምጽ ማግኘት እንዳለበት የአገሪቷ የምርጫ ኮሚሽን ገልጿል።
አንድ እጩ በመጀመሪያው ዙር ማሸነፍ የሚያስችለውን ድምጽ ካላገኘ ኮሚሽኑ ሁለት የተሻለ ድምጽ ያገኙ እጩዎችን በሁለተኛ ዙር ምርጫ ያወዳድራል።
የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን የምርጫውን ውጤት ለማሳወቅ የአንድ ሳምንት ጊዜ እንደሚፈጅበት በመገለጽ ላይ ነው።
የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያሸነፈው እጩ ላለፉት 10 ዓመታት አገሪቷን ከመሩት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ስልጣኑን ይረከባል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤