የጎርፍ አደጋን በመከላከል በዝናብ አጠር አካባቢዎች ጥቅም ላይ ለማዋል መስራት ይገባል- ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ

131

ነሃሴ 3/2014/ኢዜአ/ የጎርፍ አደጋን በመከላከል በተለይም በዝናብ አጠር አካባቢዎች ጥቅም ላይ ለማዋል መስራት እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የጎርፍ ቅድመ ማስጠንቀቂያና ቅድመ መከላከል ሥራዎች ሂደትን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቢሾፍቱ ውይይት እያደረገ ነው።

በመድረኩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች እየተፈተነች መሆኗን ገልጸዋል።

በዘንድሮው ዓመት በሱማሌና ኦሮሚያ ክልሎች የተከሰተው ድርቅ በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ጠቅሰዋል።

በቅርቡም በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን እንዲሁም በአዲስ አበባ በደረሰ የጎርፍ አደጋም የሰዎች ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረትም ወድሟል ብለዋል።

በቀጣይም ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላና አፋር ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባና ሌሎችም በቀጣይ ከባድ ዝናብ ስለሚጠበቅ የጎርፍ አደጋን መከላከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመሆኑም የጎርፍ አደጋን በመከላከል በተለይም በዝናብ አጠር አካባቢዎች ጥቅም ላይ ለማዋል መስራት ይገባል ብለዋል ሚኒስትሩ።

ለዚህም አጠቃላይ ማህበረሰቡና በየደረጃው የሚመለከታቸው አካላት ለችግሩ የጋራ መፍትሄ በመፈለግ ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

በውይይት መድረኩ በቀጣይ የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የሚያስችል የጋራ ዕቅድ እንደሚወጣ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም