ኢኒስቲትዩቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከስምንት የአፍሪካ አገራት ለተወጣጡ የጸጥታ አካላት 'በድህረ ግጭት ማገገሚያ' ዙሪያ ስልጠና መሰጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ኢኒስቲትዩቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከስምንት የአፍሪካ አገራት ለተወጣጡ የጸጥታ አካላት 'በድህረ ግጭት ማገገሚያ' ዙሪያ ስልጠና መሰጠት ጀመረ
ነሃሴ 2/2014/ኢዜአ/ በኢፌድሪ መከላከያ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሠላም ድጋፍ ማሠልጠኛ ኢኒስቲትዩት (አይ.ፒ.ኤስ.ቲ.አይ) ኢትዮጵያን ጨምሮ ከስምንት የአፍሪካ አገራት ለተወጣጡ የጸጥታ አካላት 'በድህረ ግጭት ማገገሚያ' ዙሪያ ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡
ስልጠናው ከጃፓን መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የቴክኒክ ድጋፍ የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በሥልጠናው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከኮንጎ፣ ጂብቲ፣ ኤርትራ፣ ኡጋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና እና ከቡሩንዲ የተወጣጡ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ፖሊስ አባላትና ሲቪሎች እንደሚሳተፉም ተገልጿል፡፡
በስልጠናው መክፈቻ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኢፌድሪ መከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ፤ ሰልጠናው ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የሰላም ማስከበር ግዳጅ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡
ሰልጠናው በሙያው ብቁ የሆነ፣ ዓለም አቀፍ ህጎችን የሚረዳና ግዳጁን በብቃት የሚወጣ ወታደር ለመፍጠር እንደሚረዳም ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ለምትወጣው ሰላም ማስከበር ግዳጅ ሰፊ አስተዋጽኦ ያለው ሰልጠና መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ለልምድ ልውውጥና አብሮ ለመስራት የተለያዩ ስምምነቶች ላይ ለመድረስም የሚረዳ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በበኩላቸው፤ ኢኒስቲትዩቱ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የሰልጠና ማዕከል መሆኑን ጠቁመው፣ የሚያደርጉትን ድጋፍም አጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጃፓን ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ሁሌም ትሰራለች ያሉት አምባሳደሯ ለዚህም አዲስ አሰራር እያስፋፋች መሆኗንም ተናግረዋል፡፡
ለተቋሙ የሚያደረጉት ድጋፍም ለመላው አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት መስፈን የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ሠላም ድጋፍ ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ሰብስቤ ዱባ፤ ለሁለት ሳምንታት የሚሰጠው ስልጠና "በድህረ ግጭት ማገገሚያ" ላይ ትኩረት ያደርጋል ብለዋል፡፡
በሰልጠናው ከመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ከፖሊስ እና ሲቪሎች የሚሳተፉ መሆናቸውን ገልጸው ይህም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ8 የአፍሪካ አገራት የተወጣጡ 34 አባላት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሰልጣኞች በቆይታቸው የጸጥታ ተቋማትን ሪፎረም፣ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ህጎች ዙሪያ እና በግጭት ወቅት እንዴት ህጻናት እና ሴቶችን መከላከል እንደሚቻልና በመሳሳሉ ርዕሶች ዙሪያ ግንዛቤ የሚጨብጡ መሆኑም ተገልጿል፡፡