ቀጥታ፡

በ60 ቀናት የተገነቡ 57 ፕሮጀክቶች በአዲስ አበባ ተመረቁ

ነሐሴ 02 ቀን 2014(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በ60 ቀናት የተገነቡ 57 ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመረቁ።

አድዋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የምገባ ማዕከል፣ ፓርኮች፣ የክፍለ ከተማ የአስተዳደር ህንፃ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት፣ ሰባት ፖሊስ ጣቢያዎች፣ የአደባባይ ማስዋብ ፕሮጀክቶች፣ የዳቦ ፋብሪካና ሱቆች ዛሬ ከተመረቁት ውስጥ ናቸው።

የዛሬውን ጨምሮ በዚህ ዓመት 334 ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸው የተገለጸ ሲሆን በህብረተሰቡ፣ በበጎ አድራጊ ባለሃብቶች ትብብር ደግሞ ከ300 በላይ ፕሮጀክቶች መሰራታቸውም ተነግሯል።

ፕሮጀክቶቹን በመረቁት ወቅትየአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዳሉት ፕሮጀክቶቹን በመገንባት ሂደት ፤ህዝቡ ከጎደሎው እያወጣ በየአካባቢው ተሳትፎ ማድረጉ በእጅጉ የሚያኮራ ነው ብለዋል፡፡

እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል እሳቤ ብዙ ፕሮጀክቶች ተጀምረው ጥለው የተሄዱና የህዝብ ሃብት በማባከን ብዙ ጉዳት አድርሰዋል ያሉት ከንቲባዋ በየአካባቢው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለቅመን በመስራት አጠናቀን ለህዝብ ጥቅም አውለናል ብለዋል፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች ትርጉማቸው ብዙ ነው ያሉት ከንቲባዋ ክፍለ ከተማው በተለያየ ቦታ ለቢሮ ኪራይ ሲከፍል የነበረውን ገንዘብ በማስቀረትና ህዝቡን ከመጉላላት ያድናል ነው ያሉት።

ፕሮጀክቶቹን በስኬት ለማጠናቀቅ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎችን የጎደለውን በመሙላት ላደረገው አስተዋፅኦ እናመሰግናለንም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም