በአፋር ክልል ጭፍራ ወረዳ በጣለዉ ከፍተኛ ዝናብ በተለያዩ የቤት እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ

215

ሐምሌ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአፋር ክልል ጭፍራ ወረዳ በጣለዉ ከፍተኛ ዝናብ በተለያዩ የቤት እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ተገለጸ።

የክልሉ አደጋ መከላከልና ስጋት አመራርና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ዳይሬክተር አቶ አይዳሂስ ያሲን  ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከትናንት በስቲያ  ከምሽቱ 1 ሰአት ጀምሮ  ሌሊቱን ሙሉ በጣለው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ምክንያት 13 ሺህ 834 ፍየል እና በግ፣ 180 የቀንድ ከብት፣ 20 ግመሎችና 3 አህዮች ሞተዋል።

በክልሉ ባለዉ ድርቅ የቤት እንስሳዎቹ በመኖ እጥረት የተጎዱ በመሆናቸዉ ዝናቡን መቋቋም አለመቻላቸው አደጋውን የከፋ  አድርጎታል ብለዋል።

በተለይም በወረዳው ደርጌራ፣ አፉማና ወአማ ቀበሌዎች በዝናቡ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው አመልክተዋል።

የቤት እንስሳቶቻቸው ለሞቱባቸው ቤተሰቦች  ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ነው አቶ አይዳሂስ የገለጹት።

የጭፍራ ወረዳ አርብቶ አደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወግሪስ ሃፋ በበኩላቸዉ ከወረዳዉ ስፋት ጋር በተያያዘ ገና መረጃ እየተሰበሰበ የሚገኝ በመሆኑ የሞቱ የቤት እንሰሳዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም