በቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት አማካኝነት የተገነባው የልዩ ፍላጎት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
በቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት አማካኝነት የተገነባው የልዩ ፍላጎት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ

ሐምሌ 30 ቀን 2014(ኢዜአ) በቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት በ19 ሚሊዬን ብር ወጪ የተገነባው የልዩ ፍላጎት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ።
በለገጣፎ ዲቦራ ፋውንዴሽን ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባውን ትምህርት ቤት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
ትምህርት ቤቱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 19 ሚሊዬን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን ግንባታውም አንድ አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀ ነው ተብሏል።
የግንባታው ወጭ በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የተሸፈነ ሲሆን ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ 3 መቶ የሚሆኑ የአእምሮ ውስንነት ያለባቸውን ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተምራል ተብሏል።
ፅህፈት ቤቱ ያስገነባው የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት በሀገራችን የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ታዳጊዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እጥረትን በተወሰነ ደረጃ የሚቀርፍ መሆኑም ተመላክቷል።
ትምህርት ቤቱ በውስጡ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች አመቺ የሆኑ ክፍሎችና ሙሉ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ክፍሎችን የያዘ እንደሆነም ታውቋል።
የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት እስካሁን ይህንን ትምህርት ቤት ጨምሮ 24 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አስገንብቷል።
በመርሀ ግብሩ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውን ጨምሮ የዲቦራ ፋውንዴሽን መስራች አባዱላ ገመዳ እንዲሁም ሌሎች የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
የዲቦራ ፋውንዴሽን በ2011 ዓ.ም በአቶ አባዱላ ገመዳ እና ቤተሰቦቻቸው የተመሰረተ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ላለባቸው ተማሪዎች ትምህርት እየሰጠ የሚገኝ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው።
በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የአረንጓዴ አሻራ ማኖር መርሀ ግብር ተከናውኗል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ