ቀጥታ፡

ኢትዮ ቴሌኮም የዜጎች የአኗኗር ዘይቤ ላይ አወንታዊ ለውጥ የሚያመጡ አሰራርና ቴክኖሎጂዎችን መተግበሩን አጠናክሮ ይቀጥላል

ሀምሌ 30/2014/ኢዜአ/ ኢትዮ ቴሌኮም የዜጎች የአኗኗር ዘይቤ ላይ አወንታዊ ለውጥ የሚያመጡ አሰራርና ቴክኖሎጂዎችን መተግበሩን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።

ኢትዮ-ቴሌኮም ከዳሽን ባንክ ጋር ማህበረሰቡን የዲጂታል ፋይናንስ ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ የዲጂታል ፋይናንስ  አገልግሎት አስጀምሯል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የቴሌ- ብር ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ለዜጎች ተጠቃሚነት የላቀ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በተለይም መደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ላልሆነው ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚያስችል ስለመሆኑም አስረድተዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ከዳሸን ባንክ ጋር በመተባበር ያስጀመረው አገልግሎት ቴሌብር እንደ ኪሴ፣ ቴሌብር መላ (ብድር) እና ቴሌ ብር ሳንዱቅ (ቁጠባ) የተሰኙ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን አስተዋውቋል።

”ቴሌብር እንደ ኪሴ” ደንበኞች በቴሌብር አካውንታቸው ላይ በቂ ገንዘብ ባይኖራቸውም የተለያዩ አገልግሎቶችን በዱቤ ማግኘት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ”ቴሌብር መላ”  ለደንበኞች ብድር የሚቀርብበት ሥርዓት ሲሆን ”ቴሌብር ሳንዱቅ”  ደግሞ የቁጠባ አገልግሎት የሚሰጥበት አሰራር መሆኑን አብራርተዋል።

አገልግሎቱ የባንክ ተጠቃሚ ያልሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ያለ መደበኛ የባንክ ሂሳብ አሠራር በሞባይል ስልካቸው ብድር እና ቁጠባ በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የባንክ አገልግሎት ማግኘት የማይችሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ወደ መደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት በማምጣት ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል ዋና ስራ አስፈፃሚዋ።

ኢትዮ ቴሌኮም የዜጎች የአኗኗር ዘይቤ ላይ አወንታዊ ለውጥ የሚያመጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና አስራሮችን ኢትዮ ቴሌኮም ተግባራዊ ማድረጉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የዳሽን ባንክ ፕሬዚዳንት አስፋው አለሙ፤ ኢትዮጵያ የሰነቀችውን የፋይናንስ አካታችንትና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት እውን ለማድረግ ዳሽን ባንክ የበኩሉን አስተዋዕኦ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በትብበር የተጀመረው የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ደንበኞች ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በቀጣይም ባንኩ ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ማቅረቡን ይቀጥላል ብለዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው ቴሌብር አሁን በያዘው ሁኔታ የኢትዮጵያን የዲጂታል ክፍያና የመንግስት የክፍያ አገልግሎት በማሳለጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስን ለማዘመን ኢትዮ ቴሌኮም በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ብሔራዊ ባንክ  ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም