ቀጥታ፡

በ2013/2014 ምርት ዘመን ለመሰብሰብ ከታቀደው ምርት 90 በመቶውን ማሳካት ተችሏል-ግብርና ሚኒስቴር

ሐምሌ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ2013/2014 ምርት ዘመን ለመሰብሰብ ከታቀደው 374 ሚሊዮን ኩንታል 336 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በመሰብሰብ የዕቅዱን 90 በመቶ ማሳካት መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩና የክልል ግብርና ቢሮዎች የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2015 ዓ.ም ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በአዳማ እያካሄዱ ነው።

ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን መድረኩን ሲከፍቱ እንዳሉት ባለፈው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለይም በግብርናው ዘርፍ መልከ ብዙ ፈተናዎች አጋጥመዋል።

ዘርፉን በሜካናይዜሽን የታገዘ ከማድረግ አንጻር በሁሉም ክልሎች ማስጀመር መቻሉና በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

May be an image of 1 person, sitting, standing, table and indoor

በተለይም በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት በበጋ ስንዴ ልማት ጅምሮች ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም ስሟ የተመሰገነበት ውጤት ማስመዝገቧን አንስተዋል።

በእንስሳት ዘርፍም በዶሮ ልማት፣በዝርያ መሻሻልና ስጋ ልማት ጥሩ ጅምሮች ቢኖሩም መሻሻል ያለበት ነው ብለዋል።

በአገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች ከተከሰቱ ችግሮችና ፈተናዎች አንፃር ዘርፉ በአጠቃላይ የተሻለ አፈፃፀም ማሳየቱን ገልፀዋል።

በስራ ዕድል ፈጠራ፣ ኤክስፖርትና ገቢን ማሳደግ ረገድ መልካም ውጤቶች እንደተገኙና በግብርናው ዘርፍ መነቃቃት የተፈጠረበት ዓመት እንደነበር አንስተዋል።

በኤክስፖርት ዘርፍ በቡና ዘርፍ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንና በስጋ ዘርፍም የተሻለ አፈፃፀም እንደተመዘገበ ገልፀዋል።

የ2015 በጀት አመት ዕቅድ የተለጠጠ በመሆኑ ይህን ዕቅድ ለማሳካት ተቋማት ትልቅ ፈተና ይጠብቀናል ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም