ለአሸባሪው ህወሓት ድጋፍ ሊውል የነበረ 1.2 ሚሊየን ብር በላይ ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
ለአሸባሪው ህወሓት ድጋፍ ሊውል የነበረ 1.2 ሚሊየን ብር በላይ ተያዘ
ሐምሌ 30 ቀን 2014(ኢዜአ) ለአሸባሪው ህወሓት ድጋፍ በህገ-ወጥ መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ ክልል ሊገባ የነበረ 1.2 ሚሊየን ብር በላይ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ የውጪ ሀገር ዜግነት ያለው ተጠርጣሪ ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።
ተጠርጣሪው ገንዘቡን በኢንቨስትመንት ሽፋን ወደ ትግራይ ክልል መቀሌ ለማስገባት የሰሌዳ ቁጥር አ.አ ኮድ 3-A29852 ቶዮታ ዶልፊን ተሽከርካሪ በኋላ ፍሬቻና በተለያዩ የመኪናው አካል ክፍሎች ደብቆ ሲንቀሳቀስ በህብረተሰቡ ጥቆማና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አባላት ባደረጉት ጥብቅ ክትትል በቁጥጥር ሥር ሊውል ችሏል።
በፖሊስ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ለማወቅ እንደተቻለው የተያዘው ገንዘብ በትግራይ ክልል ለሚንቀሳቀሰው አሸባሪ የህወሓት ቡድን እኩይ ዓላማ ማስፈፀሚያ ሊውል የነበረ ነው።
ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ከፀጥታ አካላት ጋር ተገቢውን ቅንጅት በማድረግ በየትኛውም ደረጃ የሚወጠኑ የሽብር ተግባራትን ለመቆጣጠር የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።