ለታማኝ በየነ እና ኡዝታዝ አቡበከር አህመድ በደሴ ከተማ አቀባበል ተደረገላቸው - ኢዜአ አማርኛ
ለታማኝ በየነ እና ኡዝታዝ አቡበከር አህመድ በደሴ ከተማ አቀባበል ተደረገላቸው
ደሴ መስከረም 6/2011 ለሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ እና የሙስሊሙ ማኅበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡዝታዝ አቡበከር አህመድ ዛሬ ደሴ ከተማ ሲገቡ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡ በደሴ ሆጤ ስታዲዮም በተካሄደው የአቀባበል ስነስርዓት ወቅት ታማኝ በየነ ባደረገው ንግግር " ሀገሪቱ ለዘመናት ከቆየችበት የጭቆና ቀምበር ተላቅቃ ለዚህ የበቃችው ብዙሃኑ በከፈሉት የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ነው "ብሏል፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ እንዳለው የተጀመረውን ለውጥ በይቅርታ በፍቅርና በኢትዮጵያዊ አንድነት ማስቀጠል ይገባል፤ የመከባበር ተምሳሌት የሆነው የአካባቢው ህዝብ ለዘመናት ያቆየውን ኢትዮጵያዊ ትውፊት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል፡፡ የብዙ ተራማጅ አስተሳሰብ አፍላቂዎች መገኛ የሆነችው ደሴ ዳግም ታሪኳን እንድታድስ ማድረግ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡዝታዝ አቡበከር በበኩሉ በኃይማኖትና በብሔር ሽፋን የሚደረጉ ሸፍጦች የተጀመረውን ለውጥ እንዳያሰናክሉት ህዝቡ ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት አመልክቷል፡፡ የኃይማኖት እኩልነት የተረጋገጠባት፣ የህግ የበላይነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን መገንባት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቋል፡፡ የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር መለስ መኮነን ሁለቱ ግለሰቦች የአንድነትና የጽናት ተምሳሌት መሆናቸውን ገልጸው ለውጡ እንዲመጣ በጽናት መታገላቸውን ተናግረዋል፡፡ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆኑባትን ደሴንና ኢትዮጵያን ለማሳደግ በተለይ ከወጣቱ ኃይል ጋር በቅርበት እንደሚሰሩም አስታውቀዋል፡፡ የደሴ ከተማ ሙስሊም ማኅበረሰብ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የከተማዋ ሀገረ ስብከት ባልደረቦችና ሌሎችም አካላት ለሁለቱ ግለሰቦችና ለኢሳት ቴሌቪዥን የተለያዩ ስጦታዎችን አበርክተዋል፡፡ በአቀባበሉ ስነስርዓት በሺዎች የሚቆጠሩ የደሴና አካባቢዋ ነዋሪዎች መገኘታቸውን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል፡፡