አገራዊ የምክክር ሂደቱ ሁሉን አቀፍ እንዲሆን የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ሙያዊ ድጋፍ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ የምክክር ሂደቱ ሁሉን አቀፍ እንዲሆን የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ሙያዊ ድጋፍ ያደርጋል
ሐምሌ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) አገራዊ የምክክር ሂደቱ አካታችና ሁሉን አቀፍ ሆኖ እንዲካሄድ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ የድርሻውን እንደሚወጣ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ገለጸ።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠር በማለም መቋቋሙ ይታወቃል።
አገራዊ ምክክሩ አካታችና ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ለማስቻልም ኮሚሽኑ እየሰራ ይገኛል።
ለዚህም ስኬት የሙያ ማህበራት፣ የፖለቲካ ሊሂቃን፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ይታመናል።
ከዚህ አንፃር አገራዊ የምክክር ሂደቱ አካታችና ሁሉን አቀፍ ሆኖ እንዲካሄድ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ገልጿል።
የማህበሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሌንሳ ቢየና፤ ማህበሩ ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ጀምሮ ጠንካራ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ከሌሎች ሲቪል ማህበረሰብ ተወካይ ድርጅቶች ጋር በመሆን የሴት መብት ተሟጋቾችን ወክለው ሲሳተፉ መቆየታቸውን ጨምረዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር የሁሉም ዜጋ ጉዳይ በመሆኑ የህግ ጉዳዮች ላይ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም በአካታችነት ጉዳዮች ላይ በቅርበት እየሰራ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
በተመሳሳይ ሴቶች በምክክሩ አጀንዳ በማስያዝ በንቃት እንዲሳተፉ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ከታች ጀምሮ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ከኮሚሽኑ ሃላፊዎች ጋር በምክክሩ መካተት ስላለባቸው የሴቶች አጀንዳዎች ዙሪያ መወያየታቸውን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ሴቶች ማህበር በአገሪቱ ባሉት ስምንት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችና በሌሎች የወረዳና ዞን አደረጃጀቶች አማካኝነት ምክክሩን ለማገዝ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለቀጣይ ሶስት ዓመታት ያዘጋጀው እስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ሙያ ማህበራት የግብአትና ሙያዊ እገዛ ለማግኘት ውይይት እንደሚያደርግ የኮሚሽኑ አባላት ገልጸዋል።
አካታች አገራዊ ውይይቶች በብዙ ባለድርሻ አካላት መካከል መግባባትንና ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመፍጠር ያለመ ነው።
አገራዊ የምክክር ሂደቱ አራት ምእራፎች ያሉት ሲሆን አሁን ያለበትን የዝግጅት ምዕራፍ በተያዘው ክረምት በማጠናቀቅ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ እንደሚሸጋገር ይጠበቃል።