የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል መንግስት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ተግባራዊ እንዲያደርግ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል መንግስት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ተግባራዊ እንዲያደርግ ተጠየቀ
ሐምሌ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን፤ በዝቅተኛ ተከፋዮች ላይ የሚደርሰውን የኑሮ ጫና ለማቃለል መንግስት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ተግባራዊ እንዲያደርግ ጠየቀ።
ኮንፌዴሬሽኑ 19ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ፤ ኮንፌዴሬሽኑ ባለፉት ሶስት አመታት ለሰራተኛው መብት መከበር የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።
የደመወዝ ወለልን የሚወስን የደመወዝ ቦርድ እንዲቋቋምና በመንግስት የተዘጋጀው ደንብ ተፈትሾ ወደ ስራ እንዲገባ የበኩሉን ሚና በመወጣት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኮንፌዴሬሽኑ በዘርፉ ሳይንሳዊ ጥናት በማድረግ የኑሮ ውድነቱን ታሳቢ ያደረገ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል አዘጋጅቶ የደንቡን መፅደቅ እየተጠባበቀ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
የኑሮ ውድነቱ በተለይ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰራተኞች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቅሰው በዝቅተኛ ተከፋዮች ላይ የሚደርሰውን የኑሮ ጫና ለማቃለል መንግስት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ተግባራዊ እንዲያደረግ ጠይቀዋል።
ኮንፌዴሬሽኑ በዝቅተኛ ደመወዝ የሚተዳደሩ ሰራተኞችን ለመደገፍ ምርቶችን በቀጥታ ከአምራቹ እንዲያገኙ ከመሰረታዊ ሕብረት ስራ ማሕበራት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማስፈንና ምርታማነትን ለማሳደግ አሰሪው የኑሮ ውድነቱን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሰራተኛውን ጥቅም ማስከበር እንደሚገባውም አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት አብዛኛው በአሰሪና ሰራተኞች መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች በምክክር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
ኮንፌዴሬሽኑ ባለፉት ሶስት አመታት በ300 ተቋማት የሰራተኛ ማህበራት እንደ አዲስ እንዲደራጁ ማድረጉንም አስታውሰዋል።