የፋይናንስ ቴክኖሎጂ እድገቱ የግብርና፣ ኮንስትራክሽንና የማምረቻ ዘርፉን አጣምሮ ሊያራምድ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የፋይናንስ ቴክኖሎጂ እድገቱ የግብርና፣ ኮንስትራክሽንና የማምረቻ ዘርፉን አጣምሮ ሊያራምድ ይገባል
ሐምሌ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እድገቱ በተለይም የግብርና፣ ኮንስትራክሽንና የማምረቻ ዘርፉን አጣምሮ ሊያራምድ እንደሚገባ ተገለጸ።
የዚሁ አንድ አካል የሆነውና የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ለብሄራዊ ኢኮኖሚ ያለው ጠቀሜታ በሚመለከት የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አከናዋኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ይልቃል አባተ፤ የውይይት መነሻ ፅሁፍ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ በፋይናንስ ቴክኖሎጂ በዓመት ከሦስት መቶ ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ መዘዋወሩን ጠቅሰው ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚዘዋወረው ገንዘብ ከአገሪቱን አጠቃላይ የምርት ምጣኔ (ጂዲፒ) 10 በመቶ የሚይዝ መሆኑንም አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለየም በትራንስፖርት፣ በባንኮችና በመዝናኛው የክፍያ ስርዓት የፋይናንስ ዲጂታል ቴክኖሎጂ በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ገልጸው ለዚህም መሰረታዊ እውቀት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት መስፋፋት ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመቆጣጠር የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ወሳኝ ድርሻ እንዳለውም አብራርተዋል።
በመሆኑም በተለየም የንግዱ ማኅበረሰብ ከፋይናንስ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር የተያያዘ መሰረታዊ ዕውቀት ሊኖረው ይገባል ነው ያሉት።
የፋይናንስ ቴክኖሎጂውን ለማሳደግ ባንኮች የራሳቸውን የዳታ ማዕከል መገንባታቸውና የቴሌኮም ኦፕሬተሮችን መያዛቸው ለገንዘብ ዝውውሩ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የፋይናንስ ቴክኖሎጂው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዋነኛ ምሰሶ የሆኑትን ግብርና፣ ኮንስትራክሽንና የማምረቻ ዘርፉን አጣምሮ ሊራመድ እንደሚገባውም ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ዋና ፀሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፤ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ቀልጣፋ በማድረግ የኩባንያዎችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የማይተካ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በመቀነስ የዲጅታል ግብይትን በስፋት ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
በተለይም የንግዱ ማህበረሰብ የፋይናንስ ቴክኖሎጂው ለዘመናዊና ቀልጣፋ ግብይት እንዲሁም ለአገር እድገት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እውቀትን በማሳደግ በሰፊው እንዲተገብሩ አስገንዝበዋል።