ቀጥታ፡

ቤታችን መታደሱ ለዓመታት በዝናብና ብርድ ሲደርስብን ከነበረው ችግር ታድጎናል--ተጠቃሚ አቅመ ደከማ እናቶች

ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መኖሪያ ቤታቸው መታደሱ ለዓመታት በዝናብና በብርድ ሲደርስባቸው የነበረውን ችግር እንዳስቀረላቸው በባህር ዳር ከተማ ተጠቃሚ አቅመ ደከማ እናቶች ገለፁ።

በከተማው በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ129 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነም ተገልጿል።

በክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ቤታቸው የታደሰላቸው ወይዘሮ ነጠረች አግማስ እንደገለጹት  ቤታቸው በዕድሜ መግፋት በመጎዳቱ የዝናብ ውሃ እያስገባ ለብርድ ያጋልጣቸው እንደነበር ገልጸዋል።

አንድ ቀን በተኛሁበት በላዬ ላይ ይፈርሳል የሚል ስጋት ስለገባቸው ተረጋግተው እንቅልፍ እንደማይተኙም ነው የገለጹት

በቀን ሥራ እና በስፌት ሥራ ይተዳደሩ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት በህመም ምክንያት ስራ በማቆማቸው የ9ኛ ክፍል ተማሪ ልጃቸው ትምህርቱን ማቋረጡን ገልጸዋል።

ልጃቸው ቀን ሥራ ሰርቶ በሚያመጣው አነስተኛ ገቢ እየተዳደሩ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ነጠረች፣ የእለት ምግብ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ኑሮ እንደከበዳቸው ገልጸዋል።   

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የክረምት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማስተባበር ባላሰቡበት ወቅት ቤታቸው  በመታደሱ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

ለዝናብና ለነፋስ ይጋለጡ የነበረበት ሁኔታ አሁን መፍትሄ ማግኘቱን የገለጹት ወይዘሮ ነጠረች፣ ይህንን ሁሉ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የቤታቸው ጣሪያ በፕላስቲክ የተከለለ በመሆኑ ከዝናብ ፋሳሽ በተጨማሪ ቀን የሚወጣው ፀሐይም ሲያስቸግራቸው መቆየቱን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ባንቹ ዋለ ናቸው።

ያለአጋዥ የቀን ሥራ በመስራት ኑሯቸውን እየገፉ ያሉት ወይዘሮ ባንቹ፣ ለዓመታት ቤታቸው የቆርቆሮ ክዳን እንዲኖረው ሲመኙ መኖራቸውን ገልጸዋል።

ከዕለት ጉርስ ይልቅ የቤታቸው ሁኔታ ሲያሳስባቸው መኖሩን ገልጸው፣ ከተማ አስተዳደሩ ችግራቸውን አይቶ የላስቲክ ቤታቸው እንዲታደስ በማድረጉ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

"ቤቴ ታድሶ ዛሬ እንደ ጎረቤቶቼ ከሞቀ ቤት እንድኖር በመደረጉ እንደ አዲስ የተወለድኩ ያህል ነው የተሰማኝ'' ሲሉ ገፀዋል።

በባህር ዳር ከተማ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሳተፉ ካሉ ወጣቶች መካከል ወጣት ማስረሻ ማሬ በበኩሉ፣ እሱን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን በመጠቀም የአቅመ ደካሞችን ቤት እያደሱ መሆኑን ተናግሯል።

"አቅመ ደካሞች ሲደሰቱ ከማየት በላይ የሚገኝ እርካታ የለም" የሚለው ወጣቱ፣ "የክረምት ጊዜን በአልባሌ ቦታ ከማሳለፍ ይልቅ የአቅመ ደካማ ሰዎችን እንባ በሚያብሱ ስራዎች በማሳለፌ ደስተኛና እድለኛ ነኝ" ብሏል።

ለበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ከመጠቀም ባለፈ ገንዘብ እንደሚያሰባስቡ የገለጸው ወጣት ማስረሻ፣ ሌሎች ወጣቶችም በአካባቢያቸው መልካም ነገር በመፈጸም ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ መክሯል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ አብርሃም አሰፋ በበኩላቸው "በከተማዋ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አግልግሎት ሥራዎች 129 ሺህ ወጣቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ" ብለዋል።

በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ችግኝ ከመትከል ባለፈ የደም ልገሳ፣ የጽዳት፣ የማጠናከሪያ ትምህርትና መሰል ተባራትን እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ከ110 በላይ የአቅመ ደካሞችንና ረዳት የሌላቸውን አረጋውያን ቤቶች የማደስና በአዲስ መልክ መልሶ የመስራት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም ከ50 በላይ የሚሆኑ ቤቶችን በመጠገን የነዋሪዎችን የከፋ ችግር በመፍታት ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ አስረድተዋል።

የበጎ ፈቃድ ስራው እስከ ነሐሴ ወር መጨረሻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ እብርሃም ጠቁመው፤ ሁሉም አካል የበኩሉን ድጋፍ በማድረግ አቅመ ደካሞችን እንዲያግዝ ጥሪ አቅረበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም