የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦች የገነቡትን አንድነት በማጠናከር ለጋራ እድገት እንዲሰሩ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦች የገነቡትን አንድነት በማጠናከር ለጋራ እድገት እንዲሰሩ ተጠየቀ

ድሬዳዋ መስከረም 6/2011 የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦች ለዘመናት የገነቡትን ህብረት በመጠበቅና አንድነታቸውን በማጽናት ለተሻለ ዕድገት መስራት እንዳለባቸው አክቲቪስት ጃዋር መሀመድ ተናገሩ። ሁለቱን ህዝቦች በማጋጨት ሥልጣንና ጥቅማቸውን ለማስበቅ የሚሯሯጡ አካላትን ሴራ በማክሸፍ ለሰላምና ለብልፅግና መረባረብ እንደሚገባ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ መሐመድ አስገንዝበዋል አክቲቪስት ጁዋር መሐመድና ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ሙስጠፋ መሐመድ ዛሬ ድሬዳዋ ሲገቡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የኦሮሞና የሶማሌ ወጣቶች፣ የድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች፣ኡጋዞች፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ነዋሪዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። ከአቀባበሉ በኋላ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ዝግጅት ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት አክቲቪስትና የኦ ኤም ኤን ሥራ አስኪያጅ አቶ ጁዋር መሐመድ የፍቅር፣ የህብረት ፣የአንድነት ተምሳሌት የሆነው የድሬዳዋ ነዋሪ ላደረገላቸው አቀባበል አመስግነዋል። የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦች በሃዘንና በደስታ ለዘመናት ከተጋሯቸውና ካካበቷቸው እሴቶች በዘለል የተዋለዱና የማይለያዩ መሆናቸውን ገልጸው የኦሮሞ ህዝብ በጨቋኝ ሥርዓቶች ሲበደል የተጠለለው ወንድሞቹ የሶማሌ ክልል ሰዎች ጋር እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡ የሁለቱ ህዝቦች መጣላት ነውር መሆኑን ጠቅሰው ከአሁን በኋላ ፍቅርና አንድነታቸውን አጠናክረው የተሻለ ሰላምና ዕድገት ለማምጣት መስራት እንዳለባቸውና የኦሮሞም ሆኑ የሶማሌ ክልሎች የሁለቱም ህዝቦች የጋራ መኖሪያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ ድሬዳዋ የምስራቁ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል እንድትሆን የፍቅርና የስፖርት መፍለቂያነቷ እንዲመለስ ሌት ተቀን እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ መሐመድ በበኩላቸው ሁለቱ ህዝቦች የሚጋሯቸውና ለዘመናት የገነቧቸው እሴቶች ያላቸው ለመብቶቻቸው በመሟገት ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል። ይህን የማይነጣጠል ህዝብ በማጣላት የራስን ስልጣንና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረጉ ጥረቶችን በማውገዝና አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ ሁሉም ነዋሪ በተለይ ወጣቶች በሰከነ መንፈስ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ “አሁን በሀገሪቱ የተገኘውን ድል ለመቀልበስ የሚደረጉ ጥረቶችን በተቀናጀ መንገድ በመመከት በሁሉም ክልሎች ሰላምና፤ ልማት ፣ብልፅግናና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመገንባቱ ሂደቱን ለማሳካት መረባረብ ይገባል” ብለዋል። የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑማስን በበኩላቸው በሀገሪቱ ለተመዘገበው የለውጥ ሂደትና ለህዝቦች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ብዙ መስዋዕትነት ከተለያዩ አቅጣጫዎች እንደተከፈለበት አስታውሰዋል። ሁለቱ ህዝቦች ተጣምረው ለሰላምና ለዕድገታቸው መስራታቸውን የማይፈልጉ ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት መኖራቸውን የገለፁት ከንቲባው ባለፈው ዓመት የተፈጠረው መሰል ችግር መቼም እንዳይደገም በሰከነ መንገድ ተወያይቶ መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል። በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የሀገር ሽመግሌዎች፣ አባገዳዎች ፣ዑጋዞች ወጣቶች፣ ሴቶች በሁለቱ ህዝቦች የተጀመሩትን ጠንካራ አንድነት የመገንባት ተግባራት ለማሳካት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና አክቲቪስት ጁዋር መሐመድ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ድሬዳዋ የሚገኘውን የሶማሌ ተፈናቃዮች የሚኖሩበትን ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ጎብኝተዋል፡፡