የወጪ ምርቶችን በአገር ውስጥ በኮንቴነር አሽጎ በመላክ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የሎጂስቲክስ ወጪ ማስቀረት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የወጪ ምርቶችን በአገር ውስጥ በኮንቴነር አሽጎ በመላክ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የሎጂስቲክስ ወጪ ማስቀረት ተችሏል
ሐምሌ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የወጪ ምርቶችን በአገር ውስጥ በኮንቴነር አሽጎ በመላክ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የሎጂስቲክስ ወጪ ማስቀረት መቻሉን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ተናገሩ፡፡
ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ የ2014 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ በርካታ ፈተናዎችን ተቋቁሞ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡን መገምገሙ ይታወቃል፡፡
በተለይ በወጪ ንግድ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱ የተገለጸ ሲሆን፤ በዘርፉ የሚሰሩ ባለድርሻ ተቋማት ያከናወኗቸው የለውጥ ስራዎች ለገቢው መሻሻል ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ነው የተባለው፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍም የሎጅስቲክስ ስትራቴጂን ተግባራዊ በማድረግ የወጪ ንግድ ሂደቶች እንዲሳለጡ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱ ተመላክቷል፡፡
ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም ወደ ወጪ ንግድ ከሚቀርቡ ምርቶች ውስጥ 8 በመቶ ያህሉ ብቻ በአገር ውስጥ በኮንቴነር ታሽገው ይላኩ ነበር።
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸውን ምርቶች በውጭ ምንዛሬ በመክፈል በውጭ አገራት በኮንቴነር መታሸጉ ለሎጂስቲክስ ከፍተኛ ወጪ እንዲወጣ ከማድረጉም በላይ የምርት ጥራት ላይ እክል ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ አጠቃላይ ምርቶች 64 በመቶ የሚሆኑት በአገር ውስጥ በኮንቴነር ታሽገው መቅረባቸውን ተናግረዋል።
በተለይ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ 98 በመቶ የሚሆነው የቡና ምርት በአገር ውስጥ አቅም በኮንቴነር በማሸግ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመርከቦች የወደብ ላይ ቆይታን ከ15 ቀናት ወደ 12 ቀናት ዝቅ በማድረግ ወጪ መቆጠብ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂን ወደ ስራ በማስገባት በአጠቃላይ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉን ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆነው የ2014 በጀት ዓመት አፈጻጸም መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን በበኩላቸው ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት የግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በተለይ የቡና ምርት ወጪ ንግድ ሎጂስቲክስን ለማሳለጥ የተከናወኑ ተግባራትን በአብነት አንስተዋል፡፡
በቀጣይም አቮካዶን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ምርቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የወጪ ንግዱን አፈጻጸም ለማሻሻል እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ከግብርና ምርቶች ባሻገር የአምራች ኢንዱስትሪዎች የወጪ ንግድ አፈጻጸም እየተሻሻለ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ተናግረዋል፡፡
በዚህም በተጠናቀቀው ዓመት ዘርፉ የተለያዩ ውስጣዊና ዓለም አቀፋዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘቱን ነው የጠቀሱት፡፡
ለዚህ ደግሞ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ ሚና ማበርከታቸውን ተናግረው፤ ዘንድሮ ብቻ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 50 ነጥብ 2 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዘርፉ ከ250 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤