የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ለማሳካት በጥናትና ምርምር ሊያግዙ እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ለማሳካት በጥናትና ምርምር ሊያግዙ እንደሚገባ ተመለከተ
ሆሳዕና ፤ ሐምሌ 29/2014 (ኢዜአ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እያካሄደች ያለውን የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ለማሳካት በጥናትና ምርምር ስራዎች ሊያግዙ እንደሚገባ ተመለከተ።
በአካባቢ ህጎች ልማትንና ተከባሪነትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ማስጠበቅን ዓላማ ያደረገው ብሔራዊ የአካባቢ መብቶች ማስጠበቂያ ፎረም በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአየር ንብረት ለውጥ ክስተትን መቋቋም የሚያስችል የጥናትና ምርምር ስራዎች ይጠበቅባቸዋል።
በተለይ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አሁን ላይ እያስገኘ ካለው ፋይዳ ባለፈ ልምዱን ሌላውም ለዓለም ጭምር እንዲወሰደው መሰራት እንዳለበት አንስተው፤ በዚህ ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርብ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
እየተከናወነ ያለውን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አስተዋጽኦ ወጥና ተምሳሌት በሚሆን መልኩ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል ።
ከዘርፉ የሚገኘውን ውጤት ለትውልድ ተሻጋሪ በሆነ እንዲሁም ለዓለም ማህበረሰብ ተሞክሮ በሚሆን መልኩ ሰንዶ በማስቀመጥ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በፎረሙ የሚቀርበውን በጥናትና ምርምር የተደገፈ የአስር አመት መሪ እቅድ በማዘጋጀት ደረጃም የዋቸሞና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ልምድና ዕውቀት በማካፈል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅዋል።
ባለስልጣኑ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አካባቢን ለመፍጠር ህግ ከማውጣት ጀምሮ ስርዓት እስከማበጀት ድረስ በተቋቋመው ፎረም አማካኝነት ተቀናጅቶ በመስራት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ስራን አጠናክሮ ማስቀጠል ተመጣጣኝ የሆነ ውሃ:መሬትና አየር በማስጠበቅ የሰው ልጆች በህይወት የመኖር ጉዳይን ማረጋገጥ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ ናቸው።
ሀገሪቱን በኢኮኖሚ ተወዳዳሪና ካደጉት ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ እንዲሁም የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ስኬታማነት መረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ለአየር ንብረት የማይበገር አካባቢን መፍጠር ለሌሎች ሁሉ ልማቶች መሰረት መሆኑን አስረድተዋል።
ችግኝ ተከላ በኢትዮጵያ በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ ከባህል ጋር የመቆራኘት ልምድ እንዳለው ያነሱት አቶ አብርሃም፤ በዚህ ረገድ ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት እያሳየ ያለው ጠንካራ ተሳትፎ ከግብ ላይ እንድደርስ ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በያሉበት አካባቢ እያከናወኑት ያለውን ተሳትፎ በማጠናከር ተምሳሌት ሊሆኑ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር ፀደቀ ላምቦሬ በበኩላቸው፤ የሰው ልጆች የአየር ንብረት ለውጥ መከሰት የሚያደርሰውን ተፅዕኖ በውል ባለመረዳት ደንን እንደሚጨፈጭፉ ተናግረዋል።
በዚህም የተነሳ ለድርቅ፣ ለወንዞች መድረቅና በርካታ የዱር አራዊቶች እንዲጠፉ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
በተፅዕኖው በአለማችን እየታየ የመጣው ከፍተኛ የሙቀት መጠን መጨመር ምክንያት እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ጸደቀ፤ ከፊት ለፊታችን ያለው ጊዜ ከባድ ቢሆንም መፍትሔው በሰው ልጆች እጅ ላይ ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ለሚስተዋለው ተፅዕኖ መፍትሄ አምጪ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ በዚህ ረገድ በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ በትኩረት በመሳተፍ የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል ።
በተለይም በካምባታ ጠምባሮና በሀዲያ ዞኖች ዩኒቨርሲቲው እያካሄደ ባለው የአካባቢ ጥበቃ ስራ ገላጣ በነበሩ ቦታዎች ደኖች መመለስ በመቻላቸው ለማህበረሰቡ ከፍተኛ የግንዛቤ ማሳደጊያ ጭምር እየሆነ መምጣቱን አመላክተዋል።
በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ልምዱንና የተገኘውን ለውጥ በምርምር በማስደገፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰራ ነው ዶክተር ጸደቀ ያብራሩት።
በፎረሙ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ የህግ ትምህርት ቤቶች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የአካባቢ ጥበቃና ሌሎች የፌዴራል ተቋማት አመራሮችና ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡