ቀጥታ፡

የሃይማኖት ተቋማት ትብብራቸውን ይበልጥ በማጠናከር አርአያነታቸውን በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል

ሀምሌ 28/2014/ኢዜአ/ የሃይማኖት ተቋማት ትብብራቸውን ይበልጥ በማጠናከርና አንድነትን የሚሸረሽሩ አሰራሮችን በማስወገድ አርአያነታቸውን በተግባር ሊያሳዩ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ።

ፕሬዝዳንቷ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 14ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው።

የሃይማኖት ተቋማት በተናጠልና በጋራ ለአገራቸው ሰላምና ልማት በርካታ ተግባራት ማከናወናቸውንም በንግግራቸው አንስተዋል።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሃይማኖት እሴት በማይመጥን መልኩ ጭካኔ የተሞላባቸው ግጭቶች መከሰታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ ግጭቶች ዳግም እንዳይከሰቱና ቀድሞ ለመከላከል የሃይማኖት ተቋማት አስተምህሮ ትልቅ ቦታ እንዳለው ተናግረዋል።

የሃይማኖት ተቋማት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መልኩ ሕዝብን ማስተማርና ማስተባበር እንደሚጠበቅባቸውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ትብብራቸውን ይበልጥ በማጠናከርና አንድነትን የሚሸረሽሩ አሰራሮችን በማስወገድ አርዓያነታቸውን በተግባር ሊያሳዩ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።

"ኢትዮጵያ የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ በሰላም የሚኖርባት፣ ለሁሉም እኩል የሆነችና በነጻነት የምንኖርባት፣ የምንሰራባት  እንድትሆን ሁሉም በጋራ መስራት አለበት" ብለዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በመደገፍ ረገድ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግም  ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በበኩላቸው፤ ጉባኤው አባል የሃይማኖት ተቋማትን በማስተባበር ሰላምና ፍቅርን፣ መከባበርና መዋደድን በሃይማኖታዊ አስተምህሮ እየገነባ ይገኛል ብለዋል።

"የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ከፈጣሪ የተሰጠን ሰላምን የመስበክ ተልዕኮ እውነተኞች የሰላም አባቶች በመሆን በንቃትና በትጋት ልንሰራ ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።

ጉባኤው በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚካሄደው አገራዊ ምክክር በንቃት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑንም  አረጋግጠዋል።

የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም፤ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሃይማኖት ተቋማት መካከል መቻቻልና አብሮነት እንዲጠናከር እያከናወነ ላለው ተግባር አመስግነዋል።

የሃይማኖት አባቶች አጥፊዎችን በመምከር፣ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ የተቸገሩትን በመርዳት ጤናማና ሰላማዊ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ግጭቶችን ከመሰረቱ ለማስወገድ የሃይማኖት ተቋማትና ሁሉም ዜጋ በትብብር መሥራት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዛሬ ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የ2014 በጀት ዓመት  የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ተወያይቷል።

የሰላምና አብሮነት እሴት ግንባታ፣ የጥላቻና ሐሰተኛ መረጃን መከላከልና ሌሎች የ2015 በጀት ዓመት ዋና ዋና ትኩረቶች ውስጥ ተካተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም