ቀጥታ፡

የባንኩ ሴክተር በበርካታ የጤናማነት መለኪያዎች የተሻለ አፈጻጸም አስመዝግቧል - ዶክተር ይናገር ደሴ

ሐምሌ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ)በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የባንኩ ሴክተር በበርካታ የጤናማነት መለኪያዎች የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ የ2014 ዓ.ም ማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ትናንት የተገመገመ ሲሆን፤ በመድረኩ የተሻለ አፈጻጸም ከታየባቸው ሴክተሮች መካከል የባንኩ ዘርፍ አንዱ ነው፡፡

በዚህም የባንኩ ዘርፍ በተቀማጭ ሃብት መጠን፣ብድር በማስመለስ ምጣኔና በሌሎች የጤናማነት መለኪያዎች የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡም ነው የተጠቀሰው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ እንደሚሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የባንኮች አጠቃላይ ተቀማጭ ሃብት 1 ነጥብ 7 ትሪሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ይህም የ26 ነጥብ 7 በመቶ እድገት የተመዘገበበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለፈው አንድ ዓመት ባንኮች ብድር የማስመለስ አቅማቸውን በ48 ነጥብ 7 በመቶ ማሳደጋቸውን አብራርተዋል፡፡

ለግሉ ዘርፍ የሚያቀርቡት የብድር ምጣኔም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንና ይህም በአጠቃላይ የባንኩ ዘርፍ በተሻለ አፈጻጸም ላይ መሆኑን እንደሚያመላክት ነው የገለጹት፡፡

በሌላ መልኩ የቴሌ ብር ወደ ሥራ መግባትን ተከትሎ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት እየጎለበተ መምጣቱን ጠቅሰው፤ይህም ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር የዋጋ ግሽበቱ እንዲረጋጋ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ለግሉ ሴክተር የሚቀርበው የውጭ ምንዛሬ መጠን በቂ አለመሆን አሁንም በድክመት እንደሚነሳ ነው የተናገሩት፡፡

በቀጣይ የወጪ ንግድን ጨምሮ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን የሚያሻሽሉ ተግባራትን በማከናወን የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በበኩላቸው፤ የፋይናንስ ሴክተሩን ለማሻሻል የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች ዘርፉን ከውድቀት እንደታደጉት ይናገራሉ፡፡

May be an image of 1 person and suit

ለአብነትም ባለፉት አራት ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የባንኮች ቅርንጫፍ ቁጥር በ30 በመቶ ማደጉን አንስተው፤ይህም 82 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች የቁጠባ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል ነው ያሉት፡፡

ነገር ግን ከዓለም አቀፍ ጂኦ-ፖለቲካ መለዋወጥ ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረት አሁንም የኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል፡፡

መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን ከቀረጥ ነጻ ማስገባት (ፍራንኮ ቫሉታ) ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱንም እንዲሁ፡፡

በዚህም መንግሥት ማግኘት ከሚገባው ገቢ መካከል እስከ 50 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ ማጣቱን ነው ያብራሩት፡፡

በቀጣይም ገንዘብ ከሚፈለገው መጠን በላይ ወደ ገበያው እንዳይገባ በመቆጣጠርና ድህነትን በሚቀንሱ የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት በአገር ውስጥ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም