የመንገድ መበላሸት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያችን ላይ ችግር ፈጥሯል---የምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመንገድ መበላሸት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያችን ላይ ችግር ፈጥሯል---የምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች
ሐምሌ (ኢዜአ) 28/2014--ከነቀምቴ ቡሬ የተዘረጋውና ስድስት ወረዳዎችን የሚያገናኘው መንገድ በመበላሸቱ በኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ችግር መፍጠሩን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።
በጉቶ ጊዳ ወረዳ የኡኬ ከተማ ነዋሪ አቶ አዲሱ አበራ በሰጡት አስተያየት የመንገዱ መበላሸት በህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከእዚህ በፊት ከነቀምቴ ኡኬ 35 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመጓዝ ከ30 እስከ 35 ደቂቃ ብቻ ይወስድ የነበረው በአሁኑ ጊዜ በተለያየ መኪና ተቀባብሎ በመጓዝ ከግማሽ ቀን በላይ እየፈጀ መሆኑን ተናግረዋል።
"በቅብብሎሽ መኪና ሲኬድ የተለያዩ ቦታዎች ከመኪና ወርዶ በእግር መጓዝ የግድ በመሆኑ ለእንግልት እየተዳረግን ነው" ሲሉም ገልጸዋል።
ወይዘሮ ራሂማ ኑረዲን የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ባለው የትራንስፖርት ችግር ምክንያት ሸክማቸውን በጭንቅላታቸው፣ አንድ ሕጻን ልጃቸውን በጀርባቸውና ሌሎቹን በእጃቸው እንደያዙ በእግር ለመጓዝ መገደዳቸውን ተናግረዋል።
"ትራንስፖርት ቢገኝ እንኳ ለአጭር ኪሎ ሜትር ከተመን ውጭ እየተጠየቅን ነው" ያሉት ወይዘሮዋ፣ መንግስት ለመፍትሄው ፈጣን እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።
ቀደም ሲል ከጉቶ ጊዳ ወረዳ ሉጎ ከተማ እስከ ነቀምቴ ለመጓዝ ለትራንስፖርት 50 ብር ይከፈል የነበረው በአሁኑ ወቅት ከ150 እስከ 200 እየተጠየቁ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ዘሪቱ በቀለ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።
"እንዲህም ሆኖ በመንገዱ ብልሽት ምክንያት አብዛኛውን መንገድ እቃ ተሸክመን በእግራቸው እየተጓዝን ነው" ብለዋል።
በእዚሁ የመንገድ ችግር በአካባቢያቸው የሽንኩርት ዋጋ በኪሎ 100 ብር እየተሸጠ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ዘሪቱ፣ ይህም በኢኮኖሚያቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩንም ነው ያስረዱት።
የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪው በጭቃ ተይዞ መንገድ ላይ ሲያድር ብዙ ገንዘብ ከፍሎ እንደሚያስጠብቅና ለመኪናው ማስጎተቻም ተጨማሪ ወጪ እየከፈለ መሆኑን የተናገረው ደግሞ የሕዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪው ወጣት ጉርሜሣ ጎንፋ ነው።
በዚህ ምክንያት ለብልሽት የሚዳረጉ የመኪናው ክፍሎችን ነቀምቴ ከተማ ደርሶ ለማስጠገን ከአቅም በላይ እየሆነበትና ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ እየገባ መሆኑን ተናግሯል።
መንገዱ ለረጅም ጊዜ ጥገና ሳይደረግለት በመቆየቱ የተነሳ ለከፍተኛ ብልሽት መዳረጉን የገለጹት ደግሞ የምሥራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ገመዳ ተፈራ ናቸው።
የመንገዱ ብልሽት በዕለት ተዕለት እንቅስቀሴ ላይ ከሚያደርሰው ተጽዕኖ በተጨማሪ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖችም የዕርዳታ እህል ለማድረስ እንቅፋት ሆኗል።
ከነቀምቴ ጊዳ አያና 100 ኪሎ ሜትር መንገድ ላይ በብዙ ቦታዎች ከፍተኛ ብልሽት መከሰቱንና በቀላል መሳሪያዎች ጠግኖ ማስተካከል እንደማይቻልም ተናግረዋል።
ችግሩ የበላይ አካልን ልዩ ትኩረት እንደሚፈልግ የገለጹት አቶ ገመዳ፣ በችግሩ ምክንያት በሕዝቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኑሮ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የነቀምቴ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ቶሎሳ በበኩላቸው፣ በብልሽቱ ሕብረተሰቡን ለከፍተኛ ችግር እየተዳረገ በመሆኑ ቅሬታው ተገቢና አግባብ መሆኑን አምነዋል።
መንገዱን ወደአስፋልት ደረጃ ለማሳደግ ስራውን የተረከበው ኮንትራክተር ሥራውን አቋርጦ በመሄዱ ምክንያት ችግሩ መከሰቱንም አቶ መንግሥቱ ገልፀዋል።
"የመንገዱ ብልሽት ከዲስትሪክቱ አቅም በላይ ነው" ያሉት አቶ መንግስቱ፣ ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት ከሚደረግ ጥረት ጎን ለጎን ተጨማሪ ኃይል ለማግኘት ከበላይ አካል ጋር በመነጋግር ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በአሁኑ ጊዜ በቅርብ ያሉትን የመንገድ ጥገና መሳሪያዎች ወደስፍራው በማንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ለብልሽት የተዳረገው መንገድ ጊዳ አያና፣ ኪረሙ፣ ሊሙ፣ ጉቶ ጊዳ፣ ሐሮ ሊሙ እና ኤባንቱ የተባሉ ስድስት ወረዳዎችን እንደሚያገናኝ ታውቋል።