ቀጥታ፡

'ንባብ ለህይወት' የመጽሃፍትና የምርምር ተቋማት አውደ-ርዕይ በኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፈተ

ሐምሌ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ)'ንባብ ለህይወት' የመጽሃፍትና የምርምር ተቋማት አውደ-ርዕይ በኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፈተ፡፡

5ኛው 'ንባብ ለህይወት' የመጽሃፍትና የምርምር ተቋማት አውደ-ርዕይ በአዲስ አበባ በኤግዚቢሽን ማዕከል ነው የተከፈተው።

በአውደ-ርዕዩ ላይ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፤ደራሲያን፤መጽሐፍ አካፋፋዮችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል፡፡

አውደ ርእዩ ከዛሬ ጀምሮ ለ5 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ መሆኑም በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሀፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ይኩኖአምላክ መዝገቡ፤በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የአውደ-ርዕዩ መዘጋጀት የማሕበረሰቡን የንባብ ባህል ማጎልበትን አላማ ያደረገ ነው፡፡

በተጨማሪም በገበያ ላይ እንደ ልብ የማይገኙ መጽሐፍትን ተደራሽ ለማድረግና በአንድ ስፍራ የተለያዩ መጻሕፍቶችን በቀላሉ ማግኘት እንዲቻል ጭምር እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።

የ'ንባብ ለኢትዮጵያ' ፕሮጀክት ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ከበደ በበኩላቸው፤ በአውደ-ርዕዩ 100 የሚደርሱ ደራሲያን፤ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ስራዎቻቸውን ይዘው መቅረባቸውን ተናግረዋል።

በመርሀ ግብሩ ትረካዎች፤ የመጽሀፍት ምረቃዎች እና ሌሎች ዝግጅቶች ተካተዋል ሲሉም ገልፀዋል፡፡

የአውደ-ርዕዩ ተሳታፊ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው የአውደ-ርዕዩ መዘጋጀት አንባቢ ማህበረሰብን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም እንደ ሀገር ተመሳሳይ አውደ-ርዕይ እና ፕሮግራሞች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያሉት፡፡

አውደ-ርእዩ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሀፍት አገልግሎት ከ'ንባብ ለህይወት' ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም