ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የአገራዊ ምክክሩን ሂደት የሚከታተል ቡድን አቋቋመ

ሐምሌ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የአገራዊ ምክክሩን ሂደት የሚከታተል ቡድን ማቋቋሙን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ሊካሄድ ለታሰበው አገራዊ ምክክር አስመልክቶ ከሲቪል ማህበራት እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

ውይይቱ በመጪው ህዳር ወር ሊጀመር በታሰበው በዚሁ አገራዊ ምክክር ላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ሔኖክ መለሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሲቪል ማኅበረሰቡ አባላት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ምክር ቤቱም ዘርፉን እንዲወክል በተሰጠው ሥልጣን መሰረትም የሲቪል ማኅበረሰቡን በማንቀሳቀስ በምክክሩ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት ከሲቪል ማኅበረሰቡ የተውጣጣና አገራዊ የምክክር ሂደቱን የሚከታተል ወይም የ'ሪፈረንስ' ቡድን ማቋቋሙንም ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ጋር በመወያየትም የሲቪል ማኅበረሰቡ አባላት በምክክሩ ሂደት ውስጥ ሊኖራቸው የሚችል ሚናን መለየት መቻሉን ጠቁመዋል።

በዚህም የአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነትም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩት።

May be an image of 1 person, standing and indoor

የምክር ቤቱ የፕሮግራም እና ልማት አማካሪ ዶክተር ሞገስ ደምሴ በበኩላቸው፤ ምክክሩ የአገሪቱ ዋነኛ አጀንዳ እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ።

በመሆኑም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በዚህ አገራዊ ምክክር ላይ ለመሳተፍ እና የመፍትሔ አካል ለመሆን ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

በምክክሩም ድርጅቶቹ ለተለያዩ አገራዊ ችግሮች የመፍትሔ ሀሳቦችን በማቅረብ አስተዋጽኦ ለማድረግ እየተጉ እንደሚገኙም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም