የኢትዮጰያ ቀይ መስቀል ማህበር በምዕራብ ጎንደር ዞን ወደ ቀያቸው ለተመለሱ ተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጰያ ቀይ መስቀል ማህበር በምዕራብ ጎንደር ዞን ወደ ቀያቸው ለተመለሱ ተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ አደረገ
መተማ፣ ሐምሌ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጰያ ቀይ መስቀል ማህበር በምዕራብ ጎንደር ዞን አዳኝአገር ጫቆ ወረዳ በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው ለቆዩና ወደ ቀያቸው ለተመለሱ ወገኖች 800 ሺህ ብር የሚጠጋ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል።
በማህበሩ የጎንደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አታለል ታረቀኝ እንዳሉት፤ ተፈናቅለው ለነበሩ 500 ቤተሰቦች የህጻናት አልሚ ምግብ፣ የንጽህና መጠበቂያ፣ የተለያዩ አልባሳትና የቤት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
ከዚህ ቀደም በደባርቅ፣ ዳባት እና ጭልጋ አካባቢ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ145 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፍ መደረጉን ሃላፊው አስታውሰዋል።
በማዕከላዊና እና በምዕራብ ጎንደር ዞን ለተፈናቀሉና በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችም ከ280 በላይ ቤቶችን ገንብቶ ማስረከቡን ተናግረው፤ ሰብዓዊ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው በዛብህ በበኩላቸው በዞኑ 1 ሺህ 200 የሚጠጉ ቤተሰቦች በጸጥታ ችግር ምክንያት ተፈናቅለው መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው በተሰራ የሰላምና ማረጋጋት ስራ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደቀያቸው ተመልሰው መደበኛ የልማት ስራቸውን እንዲያከናወኑ እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፤ ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት በተቻለ መጠን ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ