መንግስት አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው- አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው- አቶ መላኩ አለበል
ሐምሌ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ)መንግስት አምራች ኢንደስትሪዎችን በማስፋፋት የዜጎችን ተጠቃሚነትና የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አስታወቁ።
የኢንደስትሪ ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በተለያዩ መስኮች ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር ውይይት እያደረጉ ነው።
በውይይቱ መክፈቻ ላይ የኢንዱስትሪ ሚንስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንዳሉት በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የኢንዱስትሪ ፓርክ ይገንባልን ጥያቄ እየቀረበ ነው።
"መንግስት የአምራች ኢንደስትሪዎችን በማስፋፋት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች በትኩረት እያከናወነ ይገኛል" ብለዋል።
እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት በሀገሪቱ የሚገኙ የኢንደስትሪ ፓርኮች ቁጥርን 22 ማድረስ እንደቻለ ጠቁመዋል።
በፓርኮቹም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ግኝት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
ለፓርኮቹ ከወጣው ወጭ አንጻር የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም እየተገኘ እንዳልሆነ ጠቁመው "ምክንያቱን ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት ባለመቻላቸው ነው" ብለዋል።
የዛሬው የውይይት መድረክ ያስፈለገው በባለሀብቱ የሚነሱ ችግሮች ዙሪያ በመወያየት የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሆነ ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ የኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ፣የጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አዘዘው ጫኔ፣ የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ በየነ በራሶና የንግድና ኢንደስትሪ ቢሮ ሀላፊ አቶ አሻግሬ ጀንበሩ እንዲሁም ባለሀብቶች እየተሳተፉ ነው።