በኡለማዎች የተዘጋጀውን "የአንድነት እና የትብብር" ሰነድ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኡለማዎች የተዘጋጀውን "የአንድነት እና የትብብር" ሰነድ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው
ሐምሌ 28 ቀን 2014(ኢዜአ) በኡለማዎች የተዘጋጀውን “የአንድነት እና የትብብር” ሰነድ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ገለጹ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የሕዝበ-ሙስሊሙን መብትና አንድነት ለማስጠበቅ መስዋዕትነት ተከፍሏል።
“አንድነት ኃይል፣ ሰላም፣ ዲን፣ በረካ እና ልማት” በመሆኑ ለሕዝበ-ሙስሊሙ ብሎም ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
“መለያየት ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም” የሚሉት ፕሬዝዳንት ሼህ ኢብራሂም፤ ሕዝበ-ሙስሊሙ ለመብቱና አንድነቱ የከፈለውን መስዋዕትነት ውጤታማ ለማድረግ በትብብር ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሕዝበ-ሙስሊሙን አንድነትና ትብብር የሚያጎለብቱ ጉዳዮችን ትኩረት ሰጥቶ ይሰራልም ብለዋል፡፡
በመሆኑም ለኢትዮጵያና ሕዝበ-ሙስሊሙ አንድነትና ሰላም በሚበጅ መንገድ በኡለማዎች የተዘጋጀውን “የአንድነት እና የትብብር” ሰነድ ገቢራዊ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ለአገር ሰላም የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክት ትውልድ ለመፍጠር መጅሊሱ ምሁራን፣ ወጣቶችና ሴቶችን በማሳተፍ የሚጠበቅበትን ሥራ ያከናውናል ብለዋል፡፡
በውጭ ሀገር ያሉ ግለሰቦች እና ድርጅቶች የሚስተናገዱበት ቢሮ በመክፈት ለአገር አንድነትና ሰላም ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል ፡፡
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ