በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ተካሄደ
ባህር ዳር፣ ሐምሌ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የድጋፍ ስምምነት ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ተካሄደ።
በፕሮጀክቱ በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ማቋቋምን ጨምሮ የተለያዩየህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት የሚከናወኑ ሲሆን 253 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለታል።
የድጋፍ ስምምነት ፕሮጀክቱ ስምንት ሃገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር የሚተገበር እንደሆነም ተጠቁሟል።
ድጋፉ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው 32 ትምህርት ቤቶችን፣ 17 ጤና ተቋማትንና ሌሎች የግብርና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚውል ነው ተብሏል።
በዚህም ለተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችድጋፍ የሚደረግ ሲሆን ለተቋማቱ ደግሞ የትምህርት፣ የህክምናና የግብርና ቁሳቁሶች ድጋፍ ይደረጋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ሰጭ ዳይሬክተር አቶ ጀበሩ ደሴ እንዳሉት በጦርነቱ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ነገር ግን ከችግሩ ስፋት አንጻር የአጋር አካላት ድጋፍ ወሳኝ እንደሆነ ገልጸው፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በዚህ ፕሮጀክት ድጋፍ ከሚያደርጉት የልማት ድርጅቶች መካከልም የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን የልማት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን የልማት ኮሚሽንና ሌሎች ድርጅቶች የሚገኙበት ሲሆን የገንዘብ ምንጫቸውም ኮምባሽን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ መሆኑ ተመላክቷል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤