ቀጥታ፡

ከወጪ ንግድ በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገበው ስኬት ለማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም መሻሻል ጉልህ ሚና ተጫውቷል-የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባላት

ሐምሌ 28 ቀን 2014(ኢዜአ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገበው ስኬት ለማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም መሻሻል ጉልህ ሚና መጫወቱን የብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባላት ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ የ2014 ዓ.ም ማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት ተገምግሟል፡፡

በዚህም በበርካታ የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡ የተገለጸ ሲሆን፤ በተለይ የወጪ ንግድ አፈጻጸሙ ከፍተኛ መሻሻል ከታየበት ዘርፍ ዋነኛው መሆኑ ተገልጿል፡፡

የወጪ ንግድ በተጨማሪ በሰው ተኮር የልማት ስራዎችም የተሻሉ ተግባራት መከናወናቸው ነው የተገለጸው፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታና  የብሔራዊ  ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባል  ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ፤ "በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል፤ ይህም ፍሬ ማፍራቱ በተግባር ታይቷል" ነው ያሉት፡፡

በተለይ  የወጪ ንግዱ በተወሰኑ ምርቶች ላይ ብቻ ጥገኛ እንዳይሆን የወጪ ምርቶችን በአይነት፣ ብዛትና ጥራት ለማሻሻል ከፍተኛ ተግባር መከናውኑን አብራርተዋል፡፡

በዚህም ከቡና ምርት ከተገኘው ገቢ ባሻገር በማዕድንና ሌሎች ዘርፎች የተሻለ ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው፤ ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የማእድን ምርት ወጪ ንግድ በአማካኝ በ64 በመቶ ማደግ ችሏል ነው ያሉት፡፡

ይህም ኢትዮጵያ የገጠሟትን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ተቋቁማ የተሻለ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም እንድታስመዘግብ ጉልህ ሚና ተጫውቷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለባትን እዳ በተገቢው መልኩ እየከፈለች መሆኑን በማስረዳት ይህም በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ የተፈጠረውን አቅም እንደሚያመላክት ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚና የብሔራዊ  ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባል አቶ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው ባለፈው አንድ ዓመት በወጪ ንግድ ከዚህ ቀደም ከተመዘገበው በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር  የሚበልጥ ገቢ ማግኘት መቻሉን አብራርተዋል፡፡

May be an image of 1 person, standing, suit and outdoors

ኢትዮጵያ አሜሪካ ለአፍሪካ የሰጠችው ከቀረጥ ነጻ እድል (አጎዋ) ክልከላ ውስጥ ሆናም እንኳ የማኑፋቸሪንግ  ዘርፍ የወጪ ንግድ አፈጻጸም በ26 በመቶ ማደግ ችሏል ነው ያሉት፡፡

ከቡና ምርት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች ላይ የተመዘገበውን ስኬት ይበልጥ ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ ባለፈው አንድ ዓመት ከመደበኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ስራዎች ባሻገር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበርካታ ገንዘብ የሚገመቱ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ 8 ሺህ የአዳዲስ ቤቶች ግንባታና የ70 ሺህ ቤቶች እድሳት መከናወኑን ጠቅሰው፤ ይህም የልማት ስራዎች አካታች እንዲሆኑ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም መንግስት ለልማት ስራዎች የሚያወጣውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ማስቀረት መቻሉን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት፡፡

የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በበጎ ፈቃድ የተከናወኑ ተግባራት በተባበሩት መንግስታት የጸደቁ የዘላቂ የልማት ግቦችን በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳበረከቱም ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች የተመዘገቡ ጠንካራ ጎኖችን በማጠናከርና ሌሎች ተግባራትንም በመጨመር በ2015 በጀት ዓመት የተሻለ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጻም ለማስመዝገብ ከወዲሁ ስራ መጀመሩንም ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም