ቀጥታ፡

ዜጎች ሰብአዊነትን እንዲላበሱ የሃይማኖት ተቋማት አስተምህሯቸውን በማጠናከር መስራት አለባቸው -ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ

ሐምሌ 28 ቀን 2014(ኢዜአ) ግጭቶችን ለመከላከልና ዜጎች ሰብአዊነትን እንዲላበሱ ለማስቻል የሃይማኖት ተቋማት አስተምህሯቸውን በማጠናከር መስራት እንዳለባቸው ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ አመለከቱ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 14ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ከተማ እያካሄደ ነው።

በጉባኤው ላይ የተገኙት ፕሬዝዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ የሃይማኖት ተቋማት ለአገር ሰላም እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ ዘርዝረዋል።

የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነታቸውን በመጠቀም በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶችን ለመከላከል እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

"ግጭትና ጭካኔን ለመከላከል የሃይማኖት ተቋማት ዜጎች ሰብአዊነትን እንዲላበሱ መስራት ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።

ሌብነትን፣ ሙስናን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመከላከልም የሃይማኖት ተቋማት አስተምሯቸውን በማጠናከር እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከሰላም በላይ የምንፈልገው ውድ ነገር የለም ያሉት ፕሬዝዳንቷ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ሲሉ ነው የጠየቁት።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በበኩላቸው "የአገር ሰላም በምኞትና በፍላጎት አይገኝም" በማለት የሀይማኖት አባቶች ከፈጣሪ የተሰጣቸውን የሰላም አባትነት በመጠቀም ለአገርና ህዝብ ሰላም ተከታታይ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለሚካሔደው አገራዊ ምክክር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አስተዋጽኦ ለማድረግ ጉባኤው ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

May be an image of 12 people, people standing and suit

የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱአለም የሃይማኖት አስተምሮ ለአንድ አገር የሰላም ግንባታ መሰረት መሆኑን አንስተው የሃይማኖት አባቶች ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ጉባኤው የ2014 በጀት አመት የጉባኤው የስራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የፍይናንስ አጠቃቀምና ኦዲት ሪፖርት፣ የ2015 በጀት አመት የስራና የበጀት እቅድ ላይ ይወያያል ተብሏል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም