አለርት ሆስፒታል የህፃናት የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ የቀዶ ህክምና መስጫ ማዕከል አስመረቀ

ሀምሌ 27/2014/ኢዜአ/ የአለርት ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 20 ሚሊዮን የወጣበት የህፃናት የላንቃ እና የከንፈር መሰንጠቅ የቀዶ ህክምና መስጫ ማዕከል አስመረቀ።

ለማዕከሉ ግንባታ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፤ ለህክምና ቁሳቁስ ደግሞ 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉ ተገልጿል።

የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ይህ ነው የተባለ ትክክለኛ ምክንያቶች አይታወቁም ።

በብዛት እንደ አጋላጭ መንስኤ ተደርገው የሚጠቀሱት ደግሞ በቤተሰብ ተመሳሳይ ችግር ካለ እና ከአካባቢው ተጽእኖ እንደሆነ ይጠቀሳል።

የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ በእርግዝና ጊዜ ጽንሱ ላይ በእናቱ ማህጸን ውስጥ እያለ የሚከሰት ትክክለኛ ቅርጽ ይዞ አለመፈጠር ነው።

በኢትዮጵያ የላንቃ መሰንጠቅ ላጋጠማቸው ህጻናት በበቂ ሁኔታ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም እንደሌለ መረጃዎች ያስረዳሉ።

የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ኢስማኤል ሸምሰዲን፤ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ከወሊድ ጋር ተያይዞ ሊያጋጥም የሚችል ክስተት መሆኑን ገልጸው በህጻናቱ እድገትና ማህበራዊ ህይወት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድር መሆኑንም ተናግረዋል።

ከጤና ሚኒስቴር፤ ከእስማይል ትሬን እንዲሁም ኪድስ ኦ.አር ከተባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር በሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ አራት ክፍሎችን በማደስ ስራ አስጀምሯል፡፡

የቀዶ ህክምና ከሚሰጡት ክፍሎች አንዱ የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ላጋጠማቸው ህጻናት ህክምና መስጠት የሚያስችሉ ግብአቶች እንደተሟሉለትም ገልፀዋል፡፡

አለርት ሆስፒታል በተለይ የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ላለባቸው  ህጻናት ሙሉ አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል አስገንብቶ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ሆኗል።

በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ እና የሆስፒታሉ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ፤ የቀዶ ህክምና ክፍሉ ከከንፈርና ላንቀ መሰንጠቅ ጋር ተያይዞ ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ህጻናት ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡

የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ለማስፋፋት ከተለያዩ አካላት ጋር በትብብር መስራታችንን እንቀጥላለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም