አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ሕግ የማስተዋወቅ ዘመቻ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ሕግ የማስተዋወቅ ዘመቻ ተጀመረ
አዲስ አበባ መስከረም 6/2011 የአፍሪካ ኅብረት አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠናን በተመለከተ የወጣውን ሕግ አገራት እንዲያጸድቁት የማስተዋወቅ ዘመቻ ጀመረ። ሕጉ በ22 የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት ከጸደቀ ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ በአህጉር ደረጃ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል። እስከ አሁን ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ስዋዚላንድ፣ ቻድ፣ ኒጀር፣ ጊኒና ጋና ነጻ የንግድ ቀጠናውን ያጸደቁ አገራት ናቸው። የቀሩት 15 አገራት ደግሞ እስከ ታህሳስ ወር ደርስ ለማስጸደቅ እየተሰራ መሆኑን በኅብረቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ኮሚሽነር አልበርት ሙቻንዳ ገልጸዋል። ጎን ለጎን ግብጽ ኬንያና ኡጋንዳ የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያን (ኮሜሳ)፣ የደቡብ አፍሪካ የልማት ማኅበረሰብ (ሳድክ) እና የምስራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብን የሦስትዮሽ ነጻ የንግድ ቀጠና አጽድቀዋል። ይሁንና የሦትዮሹን ነጻ የነግድ ቀጠና ለማጽደቅ 14 አገራት ሕጉን ማጽደቅ ይጠበቅባቸዋል። የኮሜሳ ዋና ጸኃፊና የሦስትዮሽ ነጻ የነግድ ቀጠና ግብረ ኃይል ሰብሳቢ፤ ጀነራል ቺሌሼ ካፕዌፕዌ የአህጉሪቱ ነጻ የንግድ ቀጠናና የሦስትዮሽ ነጻ የንግድ ቀጠና ሥራ በተቀናጀ አኳኋን መካሄድ አለበት ይላሉ። ለዚህም ደግሞ የአፍሪካ ኅብረትና የቀጠና የምጣኔ ኃብት ማኅበረሰብ ቅንጅታዊ አሰራር ሥምምነት በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። ቀጠናዊ የምጣኔ ኃብት ማኅበረሰቦች በአህጉሪቱ ደረጃ ለሚታሰበው ነጻ የንግድ ቀጠና መወጣጫ ደረጃ ናቸው የሚለውን ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተናግረዋል። በዓለም አቀፉ የንግድ ማዕከል የተዘጋጀው የንግድ መመሪያም የግሉ ዘርፍና ፖሊሲ አውጪዎች ሕጉን እንዲረዱትና ምርመራ እንዲያደርጉበት እያገዘ ነው ተብሏል።