ቀጥታ፡

በሕገ-ወጥ የደን ጭፍጨፋ ምክንያት ጉዳት በደረሰበት ኩየዋታ ተራራ በአንድ ጀምበር ከ200 ሺህ በላይ ችግኝ መተከሉ ተገለጸ

ሐምሌ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሕገ-ወጥ የደን ጭፍጨፋ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ኩየዋታ ተራራ ዛሬ በአንድ ጀምበር ከ200 ሺህ በላይ ችግኝ መተከሉን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ችግኞችን በማዘጋጀት መርሃ ግብሩን ማስተባበሯ ተገልጿል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ ኩየዋታ ተራራ በሕገ-ወጥ የደን ጭፍጨፋ ምክንያት ለከፍተኛ ጉዳት እየተዳረገ መሆኑን ገልጸዋል።

No photo description available.

አስተዳደሩ ተራራውን ወደቀደመ ሁኔታ ለመመለስ የአካባቢ ጥበቃ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝና የችግኝ ተከላው የዚሁ አካል እንደሆነ አመልክተዋል።

በሀዋሳ በተያዘው የአራተኛ ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ለከተማ ውበትና ለምግብነት የሚያገለግሉ ችግኞች ተከላ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሲዳማ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ በየነ በራሳ በበኩላቸው በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋን እየተሻሻለና የአፈር መሸርሸር እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

የመንግስት፣ የሲቪክ እና የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በአረንጓዴ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ የሚያከናውኑትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ቦርድ ሰብሳቢ ፓስተር ጌቱ አያሌው ቤተክርስቲያኒቱ ላለፉት 20 ዓመታት በወሎ፣ በንሳ፣ ጉጂ፣ አርቤጎና እና በሌሎች ተራራማና የተራቆቱ አካባቢዎች ባካሄደችው የአረንጓዴ ልማት ስራ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ደን መትከልና መንከባከብ ሃይማኖታዊ መሰረት እንዳለውና የሰው ልጅ የተሰጠውን ምድር የመጠበቅና የመንከባከብ ሃላፊነትና ግዴታ ያለበት ጭምር እንደሆነ አመለክተዋል።

በመሆኑም ሁሉም ምዕመን በያለበት አካባቢውን የማልማት፣ በደን እንዲሸፈን የማድረግና የመንከባከብ ሃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል።ዛሬ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ በአካባቢው የሚገኘው አጥቢያ ቤተክርስቲያን አባላት የእንክብካቤ ስራ እንደሚያከናውኑ ነው ፓስተር ጌቱ የገለጹት።

ኩየዋታ ተራራ በሀዋሳ ሀይቅ ዙሪያ ሎቄ አካባቢ የሚገኝ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም