ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን "ስለ ሰላምና ይቅርታ" በማለት የሶስት ቀናት ጾምና ጸሎት አወጀች

ሐምሌ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን "ስለ ሰላምና ይቅርታ" በማለት ከነሐሴ 1 ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ የሶስት ቀናት ጾምና ጸሎት አወጀች።

በሁሉም የካቶሊካዊት አብያተ ክርስቲያናትና በተቋሞቻቸው የንስሃና የይቅርታ ትምህርት እየተሰጠ እንዲደረግ ነው የታወጀው።

በጾም በጸሎትና በይቅርታ መንፈስ የእምነቱ አባቶችና አማኞች እንዲያከናውኑ ቆሞሳት እና ካህናት ለምዕመናኑ ጥሪ እንዲያስተላልፉ ቤተክርስቲያኗ አሳስባለች።

በመሆኑም ከነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የእምነቱ ተከታዮች በቅንነት መንፈስ ከልባቸው እንዲጸልዩ፣ የፈጣሪያቸውን ምህረትና እርዳታ እንዲጠይቁ ጥሪ ቀርቧል።

በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ለሚደረገው አስቸኳይ እርዳታ ቤተክርስትያኗ የምታደርገውን እገዛ አጠናክራ ትቀጥላለች ተብሏል።

ቤተክርስትያኗ ተፈጥሮን የመንከባከብ ሃላፊነት ከስብከተ ወንጌል ስራ በተጓዳኝ የሚሰራ መሆኑን ታምናለች።

በመሆኑም ሁሉም ምዕመን አገር በቀል ዛፎችን በየተቋማቱና በየቤቱ በመትከል፤ የአካባቢ ንጽህናን በመጠበቅ ወንድማማችነትና እህትማማችነት የበለጠ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርባለች።

በሰላም ግንባታ ስራዎች በቅንነት በመሳተፍና በተፈጥሮ ያለውን መስተጋብር እንዲጠናከር ቤተክርስትያኗ ሃላፊነቷን እንደምትወጣም አስታውቃለች።

በአገሪቱ መንግስትና ህዝብ እየተከናወነ ያለው ተፈጥሮን የመንከባከብ ንቅናቄ ትልቅ ዕድል በመሆኑ ሁሉም በፍቅር እንዲሳተፍ ቤተክርስቲያኗ ጥሪ አቅርባለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም