ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው ድንበር ተሻጋሪ ወንጀለኞችን ለመከላከል የፖሊስ አቅም ማጎልበቻ ስልጠና በመስጠት ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው

ሐምሌ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀለኞችን ለመከላከል የሚያስችል የፖሊስ አቅም ማጎልበቻ ስልጠና በመስጠት ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የላቀ የመሪነት ሙያ ያላቸው፣ ፖሊሳዊ ስነ-ምግባር የተላበሱ ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ ይገኛል።

በአገር ውስጥ ወንጀልን ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት ባሻገርም በጎረቤት አገራት የሚገኙ የፖሊስ ተቋማት ጠንካራ ቁመና እንዲኖራቸው የበኩሉን በመወጣት ላይ ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መስፍን አበበ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከአገር አልፎ በአፍሪካ ለፖሊስ ሙያ እድገት እየሰራ ይገኛል።

በምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ መኮንኖች ትብብር ድርጅት የትምህርትና ስልጠና የልህቀት ማዕከል ሆኖ እንዲደራጅ የተሰጠውን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአፍሪካ ድንበር ዘለል ወንጀለኞችን ለመከላከል የሚያስችል የፖሊስ አቅም ማጎልበቻ ስልጠና በመስጠት ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የሶማሊያ ፖሊስ ተቋም እንደ አዲስ ሲደራጅ መኮንኖችንና አመራሮቹን በማሰልጠን ጠንካራ ተቋም እንዲመሰረት ማስቻሉን ተናግረዋል፡

፡የደቡብ ሱዳንን የፖሊስ አመራሮችም በሁለት ዙር በማሰልጠን የማጠናከር ስራ ሰርቷል ብለዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ መኮንኖች ትብብር ድርጅት 14 አባል አገራትን ያቀፈ ሲሆን የፖሊስ ተቋማትን ትብብር በማጠናከር በዋነኝነት ድንበር ተሻጋሪ ወንጀለኞችን ለመከላከል ይሰራል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓሉን በማክበር ላይ ይገኛል፡፡

ዩኒቨርሲቲው እ.አ.አ በ2030 ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የፖሊስ ዩኒቨርስቲ የመሆን ራዕይ ይዟል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም