ቀጥታ፡

በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለ148 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል-የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት

ሐምሌ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ2014 በጀት አመት በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለ148 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ።

በተያዘው በጀት አመትም ከ4 ሺህ 60 በላይ አምራች ኢንተርፕራይዞችን ለማቋቋም ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዱልፈታ የሱፍ፤ በ2014 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም የተያዘውን በጀት አመት እቅድ በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የማልማትና ቀደም ሲል የተቋቋሙትንም ድጋፍ በማድረግ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

የስራ እድል በመፍጠርና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን በማዳን ዘርፉ የላቀ አስተዋጽኦ እንደነበረውም ጠቁመዋል።

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት አመት 2 ሺህ 761 አዲስ አምራች ኢንተርፕራይዞች ሲቋቋሙ ለ148 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን አስታውሰዋል።
በ2014 በጀት ዓመት ከዘርፉ ልማት ከ31 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ገልጸዋል።

በ2015 በጀት ዓመት በዋናነት “በኢትዮጵያ ታምርት” እንቅስቃሴ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ 4 ሺህ 62 አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን ለማቋቋም ታቅዷል ብለዋል።

የኢንዱስትሪውን ምርታማነትንም 65 በመቶ ለማሳደግ መታቀዱን ጠቅሰው፤የኢንዱስትሪ ተጠቃሚ ኢንተርፕራይዞች ስልጠና ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች ይሰጣሉ ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም