ኢትዮጵያ ለዓለምና ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች -ዶ/ር አብርሃም በላይ

575

ሐምሌ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለዓለምና ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ፡፡

የመከላከያ ሚኒስትሩ በቻይና አዘጋጅነት በተካሄደው የቻይና-አፍሪካ የሚኒስትሮች የሰላምና የፀጥታ ፎረም ላይ ተሳትፈዋል፡፡

ሚኒስትሩ በፎረሙ ባስተላለፉት መልዕክት ወቅቱ በዓለማችን ሆነ በአካባቢያችን የሚታዩ የጸጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሰላም ሃይሎች ጋር በትብብር መስራት የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡

የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያም በፓን-አፍሪካን መንፈስ አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካውያን ለመፍታት እንዲቻል በጽናት እየሰራች መሆኗን አስረድተዋል፡፡

የቻይና ሪፐብሊክ መንግስት አካታችና ሚዛናዊ አካሄድን በመከተል ለዓለም ሰላምና መረጋጋት እያደረገ ላለው ሚና ያላቸውን ክብርና አድናቆት ገልጸዋል፡፡

“የጋራ ደህንነትን ለማረጋገጥ አብሮነትና ቅንጅትን ማጠናከር ይገባል” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው 2ኛው የቻይና-አፍሪካ የሚኒስትሮች የሰላምና የፀጥታ ፎረም ከ50 በላይ ሚኒስትሮችና የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች መሳተፋቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም