በደቡብ ክልል በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሲያስተምሩ የነበሩ መምህራን ላይ እርምጃ ተወሰደ

107

ሐምሌ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሲያስተምሩ የነበሩ 34 መምህራን ላይ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ የትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የአዲሱ የስርዓተ ትምህርት ትግበራ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በወላይታ ሶዶ ከተማ ዛሬ አካሄዷል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ ስርዓተ ትምህርቱ በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በክልሉ በተመረጡ 134 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ መተግበሩን ገልጸዋል።

ስርዓተ ትምህርቱን የተመለከተ ስልጠና ለመምህራኑ መሰጠቱንና ያላቸው የትምህርት ዝግጁነት ላይ ማጣራት መደረጉን ተናግረዋል።

በተደረገው ማጣራት 34 መምህራን በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሲያስተምሩ መገኘታቸውን አመልክተዋል።

መምህራኖቹ ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው መደረጉን ነው ዶክተር ዲላሙ የገለጹት።

በመምህራን የቅጥር ስርዓት ላይ መሰረታዊ የሆነ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተያያዘም በደቡብ ክልል በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አዲሱን የስርዓተ ትምህርት ትግበራ በሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ትግበራና የቴክኖሎጂ አቅርቦት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ስምዖን በበኩላቸው ለአዲሱ ስርዓት ትምህርት ትግበራ ከ26 ሚሊዮን በላይ መጽሐፍት እንዲሁም ለመጽሐፉ ሕትመት ደግሞ ከ4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የሕትመት ዋጋ ንረት እና የውጪ ምንዛሪ እጥረት ማጋጠሙን አመልክተዋል።

የደቡብ ክልል መንግስት የተጠቀሱትን ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን መፍትሔ ለማበጀት እየሰራ መሆኑንና ባለው የገንዘብ አቅም መጽሐፍቱን የማሳተም ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በቀጣይ የአዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ወደ ትግበራ ለማስገባት ከ90 ሺህ በላይ መምህራን ስልጠና ለመስጠት መታቀዱን አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም