ቀጥታ፡

አካል ጎዳተኞች በሀገራዊ የልማት እቅዶች ላይ በንቃት በመሳተፍ ውጤት እያስመዘገቡ ነው - የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን

ሐምሌ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) አካል ጉዳተኞች በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ባሉ የልማት እቅዶች ላይ በንቃት በመሳተፍ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር 10 ሺህ ችግኞችን የመትከል ዕቅድ በመያዝ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ልማትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የድርሻቸውን ሚና እየተወጡ ነው ብለዋል፡፡

ለአብነትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በተከታታይ ዓመታት ንቁ ተሳትፎ እንዳላቸው አንስተዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በሶስት ተከታታይ ዙር 10 ሺህ ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ መያዙን ገልፀው፤ ፌዴሬሽኑ አካል ጉዳተኞችን በማስተባበር ባለፉት ሦስት መርሃ ግብሮች በተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ ከተከላቸው 34 ሺህ ችግኞች አብዛኛዎቹ መጽደቃቸውን ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።

አካል ጉዳተኞች በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች በንቃት በመሳተፍ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ከሚያደርጉ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ድጋፍ ማድረጋቸውን በማስታወስ፡፡

አካል ጉዳተኞች በሀገሪቱ ሁለንተናዊ የሰላምና የልማት ጉዞ በመሳተፍ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፌዴሬሽኑ የአካል ጉዳተኞች ሀገራዊ አበርክቶ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይሰራል ነው ያሉት፡፡

አቶ ማቱሳላ መና የተባሉ አካል ጉዳተኛ በሰጡት አስተያየት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሁሌም እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ተግባሩን በማጠናከር ችግኞችን እንደሚንከባከቡ ተናግረዋል፡፡

አካል ጉዳተኝነታቸው ሳያግዳቸው እንደማንኛውም ዜጋ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ በመሳተፍ አሻራቸውን እንዳኖሩ የሚገልጹት ደግሞ አቶ አበባው ክንዴ ናቸው ፡፡

አካል ጉዳተኞች መስራትና ሀገር ማልማት እንደሚችሉ ማህበረሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም