የኢትዮጵያና የቻይና የውጭ ጉዳይ አቻ ኢንስቲትዩቶች በትብብር ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የቻይና የውጭ ጉዳይ አቻ ኢንስቲትዩቶች በትብብር ለመስራት ተስማሙ
ሐምሌ 26 ቀን 2014(ኢዜአ)የኢትዮጵያና የቻይና የውጭ ጉዳይ አቻ ኢንስቲትዩቶች - የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት እና የቻይና ህዝብ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በትብብር ለመስራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ የመጀመሪያ ውይይታቸውን በስኬት አካሂደዋል።
ቻይናና ኢትዮጵያ ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ ያስቆጠረ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን በቤይጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተባባሪነት ዛሬ የተካሄደውን የኦንላይን ውይይት የመሩት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ጠቅሰዋል።
እ.ኤ.አ በ2017 ደግሞ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ ትብብር ማደጉን አስታውሰዋል።
ባሳለፍነው ዓመት የሴኔጋል ርዕሰ-መዲና በሆነችው የዳካር ከተማ የተካሄደው 8ኛው የአፍሪካ-ቻይና የትብብር ፎረም የሚኒስትሮች ኮንፈረንስ ካስቀመጣቸው 9 ዋና ዋና የትብብር መስኮች መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አንደኛው መሆኑን ገልፀዋል።
ሁለቱ አቻ ተቋማት በተለይም በጋራ የምርምር ስራዎች፤ በመረጃ፣ በህትመትና በልምድ ልውውጥ እንዲሁም የጋራ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ተባብረው እንዲሰሩና ግንኙነታቸውን የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኤምባሲው ድጋፍ እንደማይለያቸውም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ኤክዚኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደሳለኝ አምባው ሁለቱ ተቋማት የካበተ ልምድ ያላቸው ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የሁለቱን አገራት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትልቅ አቅም አላቸው ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ አምባሳደሩ በጠቀሷቸው የትብብር መስኮች ዙሪያ ከቻይና አቻው ጋር በትብብር ለመስራት ከፅኑ ፍላጎት ጋር ዝግጁ መሆኑን መግለፃቸውን በቤይጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ፕሬዝዳንት አምባሳደር ሊ ጄ በበኩላቸው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ትልቅ ስፍራ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።
ቻይና ከአፍሪካ ጋር ለምታደርገው ትብብር ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና ያላት መሆኑን ገልፀው ተቋማቸው በቀረቡት የትብብር መስኮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
አክለውም የCOVID-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሌሎች የዓለም ሀገራት አየር መንገዶች በተለየ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ ሳያቋርጥ ቻይና እና አፍሪካን በማገናኘት የተለያዩ የሕክምና መርጃ መሳሪያዎች ለመላ አፍሪካውያን ተደራሽ እንዲሆኑ በማስቻሉ ምስጋና አቅርበው አየር መንገዱ በቻይና መንግሥት እምነት የሚጣልበት መሆኑን ተናግረዋል።