እጅ ለእጅ ተያይዘን ኢትዮጵያን ከተጋረጠባት የሰላም እጦት ፈተና ማሻገር ይገባል -ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
እጅ ለእጅ ተያይዘን ኢትዮጵያን ከተጋረጠባት የሰላም እጦት ፈተና ማሻገር ይገባል -ኮሚሽኑ
ሐምሌ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ)ከህዝብና መንግስት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ በመስራትና በመመካከር ኢትዮጵያን ከተጋረጠባት የሰላም እጦት ፈተና ማሻገር እንደሚገባ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለፀ።
ኮሚሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።በውይይቱ ወቅት የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽሩ ዶክተር ዮናስ አዳየ እንዳሉት ኢትዮጵያ እየገጠማት ያለው የሰላም እጦት ችግር በመመካከር ሊፈታ የሚችል ነው።
ከህዝብና መንግስት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ በመስራትና በመመካከር ኢትዮጵያን ከተጋረጠባት የሰላም እጦት ፈተና ለማሻገር ኮሚሽኑ እንደሚተጋም ገልጸዋል።
ስልጣንም ሆነ ሀብት በሰላማዊ መንገድ ማግኘት እንደሚቻል በመገንዘብ ሰላምን ከፊት አስቀድሞ በመስበክ የግጭት አትራፊዎችን እይታ መቀልበስ እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ከህዝብ በህዝብ ለህዝብ የተዋቀረ በመሆኑ በሁሉም ደረጃ ከሚገኙ የማኅበረሰብ አካላት ጋር በቅርበት እየተወያየ እንደሚሰራ ጠቅሰዋል፡፡
ሌላው ኮሚሽነር ዶክተር ተገኝወርቅ ጌጡ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማቸውን ጠብቀው የሰላም አየር ከዓመት እስከ ዓመት የሚተነፍሱ አካባቢዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ኮሚሽኑም የእነዚህን አካባቢዎች መልካም ተሞክሮና የሰላም መሠረታዊ ምክንያቶች በመለየት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ከማስፋፋት ረገድ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ጠቁመዋል።
"ችግሮችን ጣት ወደ ሌላ ወገን በመቀሰር ሳይሆን በጋራ ተመካክረን እንፈታለን" ያሉት ደግሞ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ናቸው።
በመሆኑም ችግሮችን በመቋቋም በተባበረ ክንድ ከህዝቡ ጋር በኢትዮጵያ ሰላምና ሀገራዊ አንድነትን የማምጣት ግብን ማሳካት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በየደረጃው የኮሚሽኑን ቅርንጫፎች በመክፈት ህብረተሰቡን በቅርበት ለማወያየትና ችግሮች በመነጋገር እንዲፈቱ ለማድረግ ኮሚሽኑ ተግቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።