ቀጥታ፡

የመጀመሪያው የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

ሐምሌ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

“ኢንተርኔት ለአካታች ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው ጉባኤ የበይነ-መረብ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞች፣ ተመጣጣኝ እና ትርጉም ያለው የበይነ-መረብ ተደራሽነት፣ የበይነ-መረብ ተደራሽነት እንደ መሰረታዊ መብት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚካሄድ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በስካይ ላይት ሆቴል በሚካሄደው ጉባኤ ኢትዮጵያ ከሕዳር 19 እስከ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ለምታካሄደው 17ኛው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ቅድመ-ሁኔታ ለማመቻቸት የተዘጋጀ መሆኑን ተገልጿል።

በዓለም አቀፍ ጉባኤው ወደ ሶስት ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ እና ጉባኤው የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃትም ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የቴክኖሎጂና የሥራ ፈጠራ ማህበራትን፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን፣ መንግስትና፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እንዲሁም የግሉን ዘርፍ በያዘው አማካሪ ኮሚቴ አማካኝነት መዘጋጀቱ ተጠቁሟል።

ጉባኤው የአካል ተሳትፎ እና በይነ መረብን በመቀላቀል እንደሚካሄድ ገልጿል።

ኢትዮጵያ 17ኛው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ እንድታስተናገድ የተመረጠችው በታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም በፖላንድ በተካሄደው 16ኛው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ ላይ እንደነበር የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም